የብሪታኒያ ተዋጊ ጄቶች በፖላንድ የኔቶ የአየር መከላከል ዘመቻን ተቀላቀሉ

ራፍ ታይፉን ባለፈው ሳምንት በፖላንድ አየር ክልል 19 የሩሲያ ድሮኖች ከታዩ በኋላ ኔቶ ያሰማራው የመጀመርያው ተዋጊ ጄት ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ራፍ ታይፉን ባለፈው ሳምንት በፖላንድ አየር ክልል 19 የሩሲያ ድሮኖች ከታዩ በኋላ ኔቶ ያሰማራው የመጀመርያው ተዋጊ ጄት ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የብሪታንያ ተዋጊ ጄቶች የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የፖላንድን አየር ክልል መጣሳቸውን ተከትሎ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን የአየር መከላከል ተልዕኮን መቀለቀላቸውን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ራፍ ታይፉን (RAF Typhoon) የተባሉት የጦር ጄቶች ከአርብ ምሽት ጀምሮ የኔቶ አባል አገራት በምሥራቅ ድንበር በኩል ያለውን ኃይል ለማጠናከር በፖላንድ መሠማራታቸው ተገልጿል።

የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በዚህ ወር በተደጋጋሚ የኔቶ አባል አገራት የአየር ክልል መጣሳቸውን ተከትሎ ውጥረት ነግሷል።

ሩሲያ የፖላንድን አየር ክልልን ከመጣሷ በፊት የሮማኒያን በመቀጠልም የኢስቶኒያን የአየር ክልሎች ጥሳለች።

ሩሲያ ጥሰቱን ማጣጣል ወይም መካድን አማራጭ አድርጋ ወስዳለች።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ጆን ሄይሊ ራፍ ተዋጊ ጄቶች "የኔቶ የአየር ክልል እንደሚጠበቅ ግልጽ መልዕክት ናቸው" ብለዋል።

አክለውም "አጋሮቻችንን ከሩሲያ ግድየለሽ ጠብ አጫሪነት ለመከላከል በዚህ ውጤታማ ዘመቻ ላይ በተሳተፉት የብሪታኒያ ምርጥ ፓይለቶች እና የበረራው ባልደረቦችን ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል።

አርብ ዕለት ምሽት ሁለት ራፍ ታይፉን ጄቶች የፖላንድን ሰማይ ለመጠበቅ ከሊንከንሻየር ተነስተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሚኒስቴሩ አክሎም ጄቶቹ ቅዳሜ ዕለት ወደ ዩኬ ከመመለሳቸው በፊት አየር ላይ ነዳጅ የሚሞላላቸው ራፍ ቮያገር (RAF Voyager) አውሮፕላን አብሯቸው በርሯል።

ኔቶ ዘመቻውን ይፋ ያደረገው እአአ መስከረም 10፣ 19 የሩሲያ ድሮኖች የፖላንድን አየር ክልል ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ነው።

ሄይሊ ከአምስት ቀን በኋላ ራፍ ብሪዝ ኖርቶንን ሲጎበኙ ዩኬ ልትሳተፍ እንድምትችል ተናግረው ነበር።

የሩሲያን ድርጊት "ግድየለሽ፣ አደገኛ እና ያልተጠበቀ" ሲሉ የገለፁት ሚኒስትሩ "አደጋ ሲገጥመን በጋራ ምላሽ እንሰጣለን" ብለዋል።

ሞስኮ በፖላንድ የሚገኙ ተቋማትን "የማጥቃት ዕቅድ እንደሌላት" አስታውቃለች።

ሩሲያ ዩክሬንን እአአ በየካቲት ወር 2022 ከወረረች በኋላ ድሮኖች እና ሚሳዔሎች አገራቱን በሚያዋሰኑ ሰማይ ላይ አልፎ አልፎ ሲታዩ ነበር።

ነገር ግን በአንድ ቀን 19 ድሮኖች በፖላንድ ሰማይ ላይ መከሰታቸው አሳሳቢ ክስተት የተባለ ሲሆን የኔቶ አባል አገራትም ለመጀመርያ ጊዜ በሩሲያ ድሮኖች ላይ እርምጃ ወስደዋል።

ፖላንድ ሦስት የሩሲያን ድሮኖች ተኩሳ ጥላለች።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ "ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ግጭት ውስጥ ልንገባ የተቃረብንበት አጋጣሚ" ሲሉ ገልጸውታል።

ሮማኒያ እአአ መስከረም 14 የሩሲያ ድሮኖች የአየር ክልሌን ጥሰዋል ያለች ሁለተኛዋ የኔቶ አባል አገር ናት።

ከዚያ በኋላ አርብ ዕለት ኢስቶኒያ ሦስት የሩሲያ ድሮኖች "ያለ ፈቃድ ለ12 ደቂቃ ያህል" የአየር ክልሏን ጥሰው ገብተው በመቆየታቸው ከኔቶ አባል አገራት ጋር አስቸኳይ ምክክር አድርጋለች።

ሩሲያ ግን የኢስቶኒያን አየር ክልል መጣሷን ክዳለች።

ሩሲያ የፖላንድን አየር ክልል ጥሳ ከገባች በኋላ በኔቶ አንቀጽ 4 መሠረት የጥምረቱን ዋነኛ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለሚወስነው የሰሜን አትላንቲክ ምክር ቤት ጉዳዩ ቀርቧል።

ከዚህ ቀደም ዩኬ እና ፖላንድ በጋራ በመሆን የጦር ጄቶቻቸውን ያሰማሩት በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመን የብሪታኒያን አየር ክልል ጥሳ ተደጋጋሚ ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት ነበር።

ሄይሊ "የራፍ ፓይለቶች እና ባልደረቦች ዳግም ከፖላንድ ጋር በጋራ ለጋራ ደህንነታችን መቆማቸው የሚደንቅ ነው" ብለዋል።

የዩኬ አየር ኃይል አዛዥ ማርሻል ሀርቭ ስሚዝ "ከኔቶ ጋር ያለን አጋርነት ጠንካራ ነው" ብለዋል።

"ንቁ፣ የተጣመርን እና ከርቀት የአየር ኃይላችንን ለማሳየት ዝግጁ ሆንን እንቆያለን" ሲሉም አክለዋል።