ኢራን ፈጽማዋለች በተባለ የሳይበር ጥቃት በዩኬ አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ለቀናት ተዘግቶ እንደነበር ተገለጸ

ኮምፒውተር ላይ የሚተይብ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ አነስተኛ የኃይል ማመንጫ በሳይበር ጥቃት ምክንያት ተዘግቶ እንደነበር ተገለጸ።

መንግሥት በዩናይትድ ኪንግደም የኤነርጂ ሥርዓት ላይ ምንም ዓይነት የተደቀነ ስጋት የለም ቢልም፣ የአገሪቱ የኤነርጂ ደኅንነት ተቋማት ግን የኃይል አቅራቢ ድርጅቶች የሳይበር ጥቃት ሊኖር ይችላል በሚል የጥንቃቄ መልዕክት ማስተላለፋቸው ተገልጿል።

ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ጥቃቱ ባለፈው ወር መፈጸሙን ገልጾ ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ወንጀሉን መፈጸማቸውን ዘግቧል።

ለደኅንነት በሚል መንግሥትም ሆነ በወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚከታተለው ብሔራዊ የሳይበር ደኅንነት ማዕከል ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ይኹን እንጂ ጥቃቱ በትልቅ የኃይል ማመንጫ ላይ የተፈጸመ አለመሆኑ ታውቋል።

ቴሌግራፍ እንደዘገበው ከሆነ የኃይል ማመንጫው ተዘግቶ የነበረው ለአራት ቀናት ነው።

የኤነርጂ መሥሪያ ቤቱ የሳይበር ጥቃቱ እክል ፈጥሮ የነበረው በአነስተኛ ጄነሬተር ላይ መሆኑን እና በአገሪቱ ሥርዓት ላይ ምንም ተጽዕኖ እንደሌለው አስታውቋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ሥርዓት ለአጭር ጊዜ ኃይል የሚያቀርቡ በርካታ አነስተኛ በጋዝ የሚሰሩ ጄኔተሮችን የያዘ ነው።

የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ሥርዓት መጠበቅ ለመንግሥት ትልቅ ፈተና ነው። መንግሥት የሳይበር ደኅንነት ደንቦቹን እያዘመነ ሲሆን፣ ለዚህ ​​ዓመት መጨረሻ የሚሆን አዲስ የኃይል አቅርቦት ፈተናን የመቋቋም አቅም ስልትም እያዘጋጀ ነው።

ኢራን ጠንካራ የሳይበር አቅም እንዳላት ይታመናል። ሆኖም፣ ከአሜሪካ ጋር በገባችው ጦርነት ምክንያት የምዕራባውያን አገራት ከቴህራን በቀጥታ ወይም ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ግንኙነት ካላቸው መዝባሪዎች ሊሰነዘሩ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን ለመመከት ዝግጅት ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ እስካሁን ድረስ ግን ጉልህ የሆነ የሳይበር እንቅስቃሴ አልታየም።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የመረጃ መንታፊዎች ድረገጾች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

ኤፍቢአይ በወቅቱ የኢራን የስለላ እና የደኅንነት ሚኒስቴር የሃንዳላ ድረ ገጾችን በመጠቀም "የሽብር ፕሮፓጋንዳ" ያሰራጫል፤ "የአገዛዙን ተቃዋሚዎች ዒላማ ለማድረግ የሥነ ልቦና ዘመቻዎችን ይከፍታል" ሲል ተናግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚዎች እንዲገደሉ ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበር ቢሮው አስታውቋል።

ሃንዳላ የየኤፍ ቢአይ ኃላፊን ፓቴልን የኢሜይል አካውንት የጠለፈው፣ ኤፍቢአይ ድረ ገጾቹን በቁጥጥር ሥር በማዋሉ እና ከእነርሱ ጋር የተያያዘ መረጃ ለሚሰጡ የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በማቅረቡ ለዚያ ምላሽ ለመስጠት ነው።

በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የሃንዳላ ቡድን በአሜሪካ የሕክምና ቴክኖሎጂ ኩባንያ - ስትሪከር ላይ ለደረሰው የሳይበር ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።