ኢራን ከኒውክሌር ተቆጣጣሪ አካል ሰነድ ሰርቃለች ስትል እስራኤል ከሰሰች

ታትሟል

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራን ከግሎባል አውቶሚክ ዋችዶግ የተሰረቀ ሰነድን ተጠቅማ በመዋሸት ኒውክሌር ስታብላላ ቆይታለች ሲሉ ከሰሱ።

ናፍታሊ ቤኔት እንደሚሉት ኢራን “ዓለምን ዋሽታለች አሁንም በመዋሸት ላይ ትገኛለች።”

መልዕክታቸውን በቪድዮ ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢራን “ዓለምን ያታለለችበት” ያሉትን ሰነድ ቅጂ አውጥተው አሳይተዋል።

ከቅጂው መካከል በፐርሺያን [ፋርስኛ] የተፃፈ ኢራን “ማምለጫ” ማዘጋጀት አለባት የሚል ፅሑፍይታያል።

ኢራን ይህን በፍፁም አልፈፀምኩም፤ ይህ የእስራኤል ሥራ ነው ትላለች።

ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔትን ወቀሳ ተከትሎ እስካሁን ከኢራን አንደበት የተሰማ ይፋዊ ምላሽ የለም።

ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በሚቀጥለው ሳምንት ስብሰባ ያደርጋል።

የኤጀንሲው ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ኢራን ውስጥ ስለተገኙ ሦስት ይፋዊ ያልሆኑ የኒውክሌር ጣቢያዎች ሪፖርት ያቀርባሉ።

ኃላፊው ይፋ የሚያደርጉትን ዘገባ ቀድሞ የተመለከተው ሮይተርስ የዜና ወኪል ኢራን ስለነዚህ ጣቢያዎች ምንም ዓይነት ማብራሪያ ለኤጀንሲው አልሰጠችም ሲል አስነብቧል።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱ “ፍትሐዊና ሚዛናዊ” አይደለም ብሏል። 

ምዕራባዊያን አገራት ኢራን የኒውክሌር ስምምነቱን ሳትጥስ አትቀርም ሲሉ ይጠርጥራሉ። ኢራን ግን ይህን ወቀሳ አጥብቃ ትቃወማለች።

እስራኤል “ኢራን የዓለምና የእስራኤል መጥፊያ ናት” ትላለች።

ኢራን በበኩሏ እስራኤል እዚህች ምድር ላይ መኖር የለባትም፤ መጥፋት አለባት የሚሉ ፅኑ አቋም አላት።

ኃያላን አራትና ኢራን በፈረንጆቹ 2015 ስምምነት ገብተው ነበር።

ስምምነቱ ኢራን ኒውክሌር ማብላላቷን ከገታች የተጣለባት የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ እንደሚነሳላት ያትታል።

ነገር ግን አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ከዚህ ስምምነት ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ስምምነቱ ባለበት ቆሟል።

ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ኢራን ያበለፀገችው የዩራኒዬም መጠን ከ2015 ጋር ሲነፃፀር በ18 እጥፍ ጨምሯል ብሏል።

የበለፀገ ዩራኒዬም ለነዳጅነት ቢያገለግልም ኒውክሌር ለማበልፀግም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

የእስራኤሉ ጠ/ሚ በቪድዮ መልዕክታቸው “በእጄ ኢራን የተጠቀመችበትን ሐሰተኛ ሰነድ ይዣለሁ” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት “አራን ከተባበሩት መንግሥታት አውቶሚክ ኤጀንሲ ሰነድ ሰርቃለች። ይህንን መረጃ ተጠቅማ ለኤጀንሲው ሐሰተኛ መረጃ ፈብርካለች” በትዊተር ላይ አስፍሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው የእስራኤል ሰላዮች ቴህራን ከሚገኝ አንድ መጋዘን ያገኙት ሰነድ ይህን ያሳያል ብለዋል።

ቤኔት እንደሚሉት የእጅ ፅሑፉ በቀድሞው የኢራን መከላከያ ሚኒስትር፣ ለሟቹ የኒውክሌር ሳይንቲስት የተላከ ነው።

ጉምቱው ኢራናዊ የኒውክሌር ሳይንቲስት ሞሕሰን ፋኽሪዛዴህ በፈረንጆቹ 2020 በሳተላይት ቁጥጥር በሚደረግለት የጦር መሣሪያ ቴህራን ውስጥ መገደላቸው ይታወሳል።

ኢራን ግድያውን እስራኤል ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ተባብራ ያቀነባበረችው ነው ትላለች።

እሰራኤል ለዚህ ግድያ ኃላፊነት ከመውሰድም ሆነ ወቀሳውን ከማስተባበል ተቆጥባለች።