ትራምፕ የፈጸሙት ወንጀል እንዳይሰማ በከፈሉት ገንዘብ ለተመሰረተባቸው ክስ ውሳኔ ሊሰጥ ነው

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ በኒውዮርክ በቀረበባቸው በገንዘብ የመደለል ክስ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ከመፈጸማቸው ከሁለት ሳምንት በፊት ጥር 2/ 2017 ዓ.ም. የቅጣት ውሳኔ ሊሰጥባቸው መሆኑን አንድ ዳኛ ተናገሩ።

ዳኛው ዡዋን ሜርካን ትራምፕ ላይ እስር፣ አመክሮ ወይም የገንዘብ ቅጣት እንደማይፈርድባቸው እና በምትኩ "እንደ ሁኔታው እንዲለቀቁ" የሚል የቅጣት ውሳኔ እንደሚያስተላልፉ ገልጸው፣ ተመራጩ ፕሬዝዳንት በአካል አልያም በቪድዮ ችሎት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተጠቅመው የቀረበባቸው ክስ ውድቅ ለማድረግ ሞክረዋል።

በፕሬዝዳንቱ ዙርያ ያሉ ሰዎች ዳኛውን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት መወሰናቸውን በመንቀፍ "ሕግ-አልባ" የሆነው ክስ "ወድያውኑ" ውድቅ መደረግ አለበት ብለዋል።

ትራምፕ በግንቦት ወር የንግድ ሰነዶችን በማጭበርበር ከተመሰረተባቸው 34 የወንጀል ክሶች ጋር በተያያዘ ለልቅ ወሲብ ፊልም ተዋናይዋ ስቶርሚ ዳንኤልስ ከከፈሉት 130,000 ዶላር ጋር በተያያዘ ተፈርዶባቸዋል።

ክሱ በ2016 የምርጫ ቅስቀሳ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ለቀድሞ ጠበቃቸው ሚካኤል ኮኸን ተመላሽ የተደረገ ገንዘብ ለመሸፋፈን ከተሞከረው ሙከራ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ገንዘቡም የወሲብ ፊልም ተዋናይቷ ከትራምፕ ጋር ስለነበራት የወሲብ ግንኙነት እንዳትናገር የተከፈለ ነበር።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ድርጊቱ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ያስተባበሉ ሲሆን፣ ክሱ ከ2024 የፕሬዝዳንት ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚያደርጉትን ዘመቻ ለመጉዳት የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

አርብ ዕለት የትራምፕ ቃል አቀባይ ዳኛው ያስተላለፉትን የቅጣት ውሳኔ "የሌለ ነገርን የማደን" አካል ነው ሲሉ ተችተዋል።

ስቲቨን ቼንግ "ፕሬዚዳንት ትራምፕ የፕሬዚዳንታዊ ሽግግሩን ሂደት በዚህ ወይም በማንኛውም የሌለ ነገርን ለማደን በሚደረግ ሙከራ ሳይደናቀፉ፣ ያለ እክል እንዲቀጥሉ እና የፕሬዚዳንቱ ወሳኝ ተግባራትን እንዲፈጽሙ ሊፈቀድላቸው ይገባል" ብለዋል።

"የቅጣት ውሳኔ ሊሰጥ አይገባም፤ እናም ፕሬዝዳንት ትራምፕም እነዚህን ማጭበርበሮች ሁሉም እስኪጠፉ ድረስ መታገላቸውን ይቀጥላሉ።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ በቅርቡ ጉዳዩን በመቃወም ባቀረቡት ማብራርያ፣ ጉዳዩ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው አብሯቸው የሚዘልቅ እና የማስተዳደር አቅማቸውን እንደሚያደናቅፍ ተከራክረዋል።

ዳኛው በበኩላቸው ትራምፕ ያላቸውን ስጋት በሚያቃልል መልኩ የቅጣት ውሳኔውን የሚያቀሉ በርካታ ምክረ ሀሳቦችን መቀበላቸውን አሳውቀዋል።

ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከል ፕሬዝዳንት ትራምፕ የስልጣን ዘመናቸውን በ2029 እስኪያጠናቅቁ እና እድሜያቸው 78 እስኪሞላ ድረስ ውሳኔውን ማዘግየት፣ አልያም የእስር ጊዜን የማይጨምር የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፍ የሚሉ ይገኙበታል።

ትራምፕ ምንም እንኳ ባይሳካላቸውም ያለመከሰስ መብት እንዳላቸውበማቅረብ ተከራክረዋል።

በሐምሌ ወር የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በስልጣን ዘመናቸው ለሚፈጽሟቸው "ይፋዊ ድርጊቶች" ከወንጀል ክስ ነጻ የመሆን መብት እንዳላቸው ወስኗል።

ይኹን እንጂ ባለፈው ወር ዳኛው ዶናልድ ትራምፕ ስቶርሚ ዳንኤልስ ከተባለችው የልቅ ወሲብ ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ይፋ ላለማድረግ በማሰብ በገንዘብ ለመደለል ባደረጉት ሙከራ ጥፋተኛ መሆናቸውን ገልፀው ነበር።

ትራምፕ በተመሰረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው በፕሬዝዳንትነት የሚያገለግሉ የመጀመርያው ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

ነገር ግን የቅጣት ውሳኔው ከተሰጠ በኋላ ይግባኝ ለማለት ሊሞክሩ ይችላሉ።

በአሜሪካ የንግድ ሰነዶችን በማጭበርበር ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ግለሰብ እስከ አራት ዓመት እስራት የሚቀጣ ቢሆንም፣ አነስተኛ ወይንም የእስራት ቅጣት የለውም።

በምርጫው ከማሸነፉቸው በፊትም የሕግ ባለሙያዎች ትራምፕ ከእድሜያቸው እና ካላቸው የወንጀል ታሪክ ጋር በተያያዘ የእስር ውሳኔ እንደማይጠብቃቸው ገምተው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ትራምፕ በ2020 ምርጫ የገጠማቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ በመሞከር እንዲሁም ከምስጢራዊ ሰነዶች ጋር በተያያዘ በቀረቡባቸው ሦስት ወንጀሎች በፌደራል እና በተለያዩ ግዛቶች ተከስሰዋል።

መጀመርያ ላይ የቅጣት ውሳኔውን ለማሰማት ሕዳር 26 ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ዳኛው ግን ትራምፕ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ቀኑን ገፍተውታል።