ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው ስፖርተኛ በጽኑ ከተጎዳ በኋላ ለጀመረው የልጆች እርዳታ 3 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ
አሜሪካን ፉትቦል እየተባለ በሚጠራው ጨዋታ፣ የቡፋሎ ቢልስ ተጫዋች የሆነው ዳማር ሀምሊን ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ በ ‘ጎፈንድሚ’ የጀመረው እርዳታ 3 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የድጋፍ ገንዘብ አግኝቷል።
ዳማር ጨዋታ ላይ ሳለ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ጨዋታው ተቋርጧል።
የ24 ዓመቱ ተጫዋች ከተጋጣሚው ጋር በመጀመሪያው የጨዋታው ግማሽ ተጋጭቶ ነው ጉዳት የደረሰበት። ድንገቴ ልብ መቆም (cardiac arrest) ከገጠመው በኋላ በሜዳው ውስጥ ሕክምና ተሰጥቶት ኋላ ላይ ወደ ሆስፒታል ተልኳል።
ዳማር በየዓመቱ በግሪጎርያን ካላንደር ለሚከበረው የገና በዓል በ ‘ጎፈንድሚ’ ገንዘብ በማሰባሰብ ይታወቃል።
ገንዘቡ ለአቅመ ደካማ ልጆች መጫወቻ አሻንጉሊት ለመግዛት የሚውል ሲሆን፣ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ በርካቶች ስለ ተጫዋቹ ጉግል ሲያደርጉ ለእርዳታ የከፈተውን ገጽ በማግኘታቸው ነው ከፍተኛ ገንዘብ የተሰባሰበው።
ተጫዋቹ ለማሰባሰብ አቅዶ የነበረው 2 ሺህ ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ከጉዳቱ በኋላ ግን በገጹ የተሰጠው ልገሳ 3 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።
በትውልድ ከተማው እርዳታ ማሰባሰብ የጀመረው ተከፋይ ተጫዋች ከመሆኑ በፊት ነበር።
ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የአሜሪካን ፉትቦል ሊግ የሆነው ኤንኤፍኤል ጨዋታውን ለአንድ ምሽት አቋርጧል።
ከተቀናቃኝ ተጫዋች ጋር ከተጋጨ በኋላ ልቡ ለተወሰነ ደቂቃ ቆሞ እንደነበርና እዚያው ሜዳ ውስጥ በተሰጠው ሕክምና በድጋሚ ልቡ መምታት እንደጀመረ ክለቡ አስታውቋል።
የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ዳማር የወደቀበት ቦታ ተሰብስበው በጭንቀት ሲመለከቱት፣ አንዳንዶችም ሲያለቅሱ እና ሲጸልዩም ታይተዋል።
የተጫዋቹ ወኪል ጆርዳን ሮኒ በትዊተር ገጹ “አሁን የልብ ምቱ ተስተካክሏል። ለመተንፈስ የሚያግዘው ትቦ ተገጥሞለታል” ብሏል።