በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በታጣቂዎች ተገደሉ

 አቶ አህመድ አሊ

የፎቶው ባለመብት, Legesse Tulu/fb

የምስሉ መግለጫ, አቶ አህመድ አሊ
ታትሟል

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አህመድ አሊ ከሚሴ ከተማ ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።

ዋና አስተዳዳሪው የተገደሉት ዛሬ አርብ ሰኔ 28/2016 ዓ.ም. በዞኑ ዋና ከተማ ከሚሴ ውስጥ በሚገኝ መስጅድ በጁምአ ሶላት ላይ ተሳትፈው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መሆኑ ተገልጿል።

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አህመድ አሊ የተገደሉት መንግሥት ሸኔ እያለ በሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች መሆኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ስለቀረበበት ክስ ያለው ነገር የለም።

የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በአቶ አህመድ አሊ ግድያ ላይ “ፅንፈኛ” ነገር ግን በግልጽ ማንነታቸውን ያልገለጻቸው አካላትን ተጠያቂ አድርጓል።

ግድያውን በተመለከተ ከአማራ ክልል መስተዳድር በወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው አቶ አህመድ የተገደሉት “የሰላም እና የአንድነት ፀር በሆኑ ፅንፈኞች በተተኮሰባቸው ጥይት ነው።”

የፌደራል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የዞኑን አስተዳዳሪ ግድያን በሚመለከት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “ለእውነት እና ለሰላም የተከፈለ ዋጋ ነው። ወንድሜ ፈጣሪ ነፍስህን በገነት ያኑራት!!” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

አቶ አህመድ አሊ የልዩ ዞኑ አስተዳዳሪ ከመሆናቸው በፊት በገዢው ፓርቲ ውስጥ እና በክልሉ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሲያገለግሉ የቆዩ የ39 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ።

ዋና አስተዳዳሪው የተገደሉበት የአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ግጭቶች ያጋጠሙበት እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገደሉበት አካባቢ ነው።

በአማራ ክልል ውስጥ ካለው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በገዢው ፓርቲ እና በአካባቢ አስተዳዳሪዎች እና በተለያዩ ደረጃዎች ላይ በሚገኙ ኃላፊዎች ላይ ጥቃት እና ግድያ ሲፈጸም ይህ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።

በልዩ ዞኑ ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች መካሄዳቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የልዩ ዞኑ አስተዳዳሪ ግድያን በተመለከተ ከአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ ላይ “ፅንፈኝነት መሪዎችን በመግደል የሚያሸንፍ ቢመስልም፤ የበለጠ ትግላችንን መራር እና ፈጣን በማድረግ እንደ ብረት የሚያጠነክረን እንጂ ወደ ኋላ የሚመልሰን አይደለም” ብሏል።