ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ የኒውክሌር ክፍል ኃላፊ ሞስኮው ውስጥ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ተገደሉ
የሩሲያ ጦር ኃይል ከፍተኛ ጀኔራል እና ረዳታቸው ሞስኮው ውስጥ በቦምብ ፍንዳታ መገደላቸው ተሰማ።
ሌተናንት ጀኔራል ኢጎር ኪሪሎቭ የኒውክሌር፣ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል መከላከያ ኃይል ኃላፊ ነበሩ።
ጀኔራሉ ማክሰኞ ጥዋት ከመኖሪያ ቤታቸው ሲወጡ ስኩተር በተባለ መሽከርከሪያ ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ መሞታቸውን የሩሲያ መርማሪ ኮሚቲ አስታውቋል።
ከሥፍራው የወጡ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት የሕንፃው መግቢያ በፍንዳታ ክፉኛ የተጎዳ ሲሆን በፍንጥርጣሪ ምክንያት ግድግዳዎች እና መስኮቶች ፈራርሰዋል። ሁለት አስከሬን የያዙ ከረጢቶችም መንገድ ላይ ይታያሉ።
ባለፈው ጥቅምት ዩናይትድ ኪንግደም ጀኔራል ኪሪሎቭ በዩክሬን ለተፈፀመው የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጥቃት ተጠያቂ ናቸው፤ አልፎም "የክሬምሊን የተሳሳተ መረጃ ስርጭት ቀንደኛ ሰው ናቸው" በማለት ማዕቀብ ጥላባቸው ነበር።
ሰኞ ዕለት የዩክሬን ሲክሬት ሰርቪስ (ኤስቢዩ) "የኬሚካል የጦር መሣሪያ በመጠቀም ተጠያቂ ናቸው" በሚል በሌሉበት ፍርድ እንደተሰጣቸው በቴሌግራም ገፁ አስታውቋል።
ሩሲያ ከዩክሬን የሚቀርቡትን ክሶች አትቀበላቸውም።
መራማሪው ኮሚቲ በሩሲያ ዋናው መርማሪ ባለሥልጣን ሲሆን "በሁለቱ የሀገር አገልጋዮች ግድያ ዙሪያ የወንጀለኛ ምርመራ ከፍተናል" ብሏል።
"መርማሪዎች፣ የሬሳ ምርመራ ባለሙያዎች እና ሌሎች ሙያተኞች ግድያው በተፈፀመበት ሥፍራ ተገኝተው እየሠሩ ነው" ብሏል ኮሚቲው።
ነባሩ ጀኔራል የተገደሉበት አካባቢ የሚኖሩ ሩሲያዊያን ፍንዳታ ከፍተኛ ድምፅ እንደነበረው ተናግረዋል።
ፍንዳታው በሞስኮው ከተማ በደቡብ ምስራቅ ክፍል ከክሬምሊን 6.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የተሰማው።
ቦምቡ በርቀት ቁጥጥር የሚሠራ ሲሆን 300 ግራም የሚመዝን ፈንጂ ውስጥ ይዞ እንደነበር የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በዩናይትድ ኪንግድ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ማዕቀብ መሠረት ኪሪሎቭ ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ እና ከሀገር ሀገር እንዳይዘዋወር ዕግድ ተጥሎባቸው ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ግንቦት ሩሲያ ኬሚካል መሣሪያ በዩክሬን "እንደ የጦር መሣሪያ" ተጠቅማለች ስትል መውቀሷ አይዘነጋም። በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ኬሚካል መሣሪያዎችን በጦርነት ጊዜ መጠቀም የተከለከለ ነው።
በውቅቱ ሩሲያ የዩናይትድ ስቴትስን ወቀሳ "መሠረተ-ቢስ" ስትል አጣጥላው ነበር።
ኪሪሎቭ የኒውክሌር፣ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል መከላከያ ኃይል ሆነው የተሾሙት በአውሮፓውያኑ 2017 ነው።
በሩሲያ መከላከያ ኃይል በተለያዩ እርከኖች ያገለገሉት ጀኔራሉ ከዩናይትድ ኪንግደም በተጨማሪ በካናዳ እና በሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።