ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለሀብት መስላ ሐሰተኛ የሚሊዮን ፓውንድ የውስኪ 'ንግድ' ያጋለጠችው ጋዜጠኛ
የቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኛ ሰማንታ ፖሊንግ ባልጠበቀችው መንገድ በአንድ መተግበሪያ አማካይነት የማጭበርበር ወንጀል አጋልጣለች። ምርመራውን እንዴት እንደጀመረችና ምን እንዳከናወነች እንዲህ ጽፋለች፦
አንድ ምሽት ቢሮ ውስጥ ተቀምጬ ነበር። የሰዎችን ገጽታ ተመልክቶ ማንነታቸውን የሚለይ መተግበሪያ (facial recognition software) አገኘሁ። ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነም መፈተሽ ጀመርኩ።
ካስክ ውስኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ኃላፊ የሆነውን ክሬግ አርች ፎቶ በመተግበሪያው አስገባሁ።
ድርጅቱ በሚሊዮን ፖውንድ የሚቆጠር ገንዘብ ያለው ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ተቋም ነው።
የኃላፊውን ፎቶ ሳስገባ ብዙም የጠበቅኩት ነገር አልነበረም። ድንገት ግን መተግበሪያው ኃላፊው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለ የተነሳውን ፎቶ አመጣልኝ።
ግለሰቡ 6.2 ሚሊዮን ፖውንድ ከተጭበረበረበት ክስ ጋር በተያያዘ መያዙን መተግበሪያው ይገልጻል። በዚህ ማጭበርበር ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ይጠቁማል።
አደገኛ ወንጀሎችን ስመረምር ዓመታት አሳልፌያለሁ። ሰው አዘዋዋሪዎች፣ ቅጥረኛ ገዳዮች፣ አደንዛዥ ዕፅ ሻጮችና ሌሎችም ወንጀለኞችን ተከታትያለሁ።
የውስኪ ጉዳይ እመረምራለሁ ብዬ ግን አስቤ አላውቅም።
በውስኪ ዘርፍ ውስጥ የተቀናጁ የወንጀል ቡድኖች እጃቸውን ማስገባታቸውን የቢቢሲ አዘጋጅ ሊየም ማክዶጋል ነግሮኝ ነበር።
መረጃ አሾልኮ የሚያቀብል (whistleblower) አግኝቷል።
ከዚህ የወንጀል ሰንሰለት ጋር በተያያዘ ስማቸው የሚነሳ የውስኪ ተቋማትን ዝርዝር ሰጠኝ። አንደኛው ተቋም ካስክ ውስኪ ነበር።
የተመሠረተው በ2021 ሲሆን በአንድ ዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ፓውንድ ማትረፉን አስታውቋል።
ሥራውን በሆንግ ኮንግ እንደሚያከናውንና ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ድርጅት እንደሆነ አድርጎ ራሱን ያስተዋውቃል። መሪው ክሬግ አርች ነው።
ድርጅቱ በተከፈተ በ12 ወራት ውስጥ አዳዲስ ቅርንጫፎች እንደከፈተና የሠራተኞች ቁጥር በእጥፍ እንደጨመረ በቃለ ምልልሶች ይናገራል።
"ቀጣዮቹ ዓመታት የሚያመጡልንን ለማየት እጓጓለሁ" ሲልም ይደመጣል።
ከግለሰቡ ጀርባ ያለውን አስደንጋጭ እውነታ ያወቅኩት በመተግበሪያው ፎቶውን ሳስገባ ነው።
እውነተኛ ስሙ ክሬግ ብሩክስ ነው። በ2019 ታስሮ ነበር።
6.2 ሚሊዮን ፓውንድ በማጭበርበር ነበር የታሰረው። በድርጊቱ አብዛኞቹ አዛውንቶች የሆኑ 350 ሰዎች ተጎድተዋል።
ከእስር ሲለቀቅ ገጽታውን ለወጠ። ስሙን ለውጢ ካስክ ውስኪን ከፈተ።
ኃላፊ መሆን ስለማይችል እጮኛውን ኃላፊ አድርጎ ሾመ።
ለክሬግ በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ የሰጡ ባለሀብቶችን አነጋገርኩ። ካስክ ምርጥ ውስኪ እንደሚሸጥና ኢንቨስት ያደረጉት ገንዘብ 13% ወይም ከዚያ በላይ ትርፍ እንደሚያስገኝላቸው ተገልጾላቸዋል።
ባለሀብቶቹ የገዙት ውስኪ እስከ አምስት እጥፍ የሚደርስ የተጋነነ ዋጋ ያለውና ትርፉም የማይገኝ መሆኑን ደረሱበት።
ገንዘባቸውን ለአጭበርባሪ ወንጀለኛ እየሰጡ መሆኑን አላወቁም ነበር። በቀደመ የወንጀል ድርጊቱ ምክንያት ድርጅቶችን እንዳይመራ የታገደ ሰው ነው።
ስለማንነቱ እየዋሸ ነበር።
እጅ ከፍንጅ ልይዘው ነበር የፈለግኩት። የለንደን ፖሊስ እየመረመረው መሆኑን ስሰማ እጅ ከፍንጅ የመያዝ ዕድሌ አለመጠኝ ብዬ አሰብኩ።
ሆኖም ግን ምርመራ እየተደረገበት ያለው ሰው ከዚያ ቀደም ታስሮ የነበረው ክሬግ መሆኑን ማንም አላወቀም ነበር።
ክሬግ ብሩክስ በሚለው ሐሰተኛ ስሙ ነበር አዲስ ምርመራ የተከፈተው። እኔ ግን ክሬግ አርች እና ክሬግ ብሩክስ አንድ ሰው መሆኑን አወቅኩ።
ካስክ ስፒሪትስ ግሎባል የሚባል ሌላ ተቋም ሲከፈት ከካስክ ውስኪ ጋር ያለውን ተመሳሳይነት አስተዋልኩ።
ሌላ ድርጅት ከፍቶ ሌሎች ባለሀብቶችን እያጭበረበረ ይሆን? ብዬ አሰብኩ። ለካስክ ስፒሪትስ ግሎባል ኢሜል ጻፍኩ።
ራሴን እንደ ሀብታም ሰው ወኪል አድርጌ አቀረብኩ። በውስኪ ንግድ ገንዘብ ማፍሰስ የሚፈልግ ባለሀብት ተወካይ ነኝ ብዬ ጻፍኩላቸው።
ክሬግ ሀችንስ የሚባል ሰው ለኢሜሌ ምላሽ ሰጠኝ። ክሬግ ብሩክስ ራሱ እንደሆነ ጠርጥሬያለሁ።
በአካል እንገናኝ አልኩት። ከሳምንታት በኋላ በካስክ ስፒሪትስ ግሎባል ቢሮ ተገኘሁ።
ክሬግን ፊት ለፊት አየሁት። ለወራት ያህል ፎቶውን ብቻ ነበር የተመለከትኩት።
በሚሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ ያጭበረበረ ሰው ነው።
ስሙን ለውጦ የድርጅቱ ኃላፊ መስሎ አዋራኝ። ካስክ ውስኪ ድርጅት ውስጥ አብረውት የሚሠሩ ሁለት ሰዎችም ነበሩ።
ክሬግ በመላው አውሮፓ 11,000 ደንበኞች እንዳሉትና ለሰባት ዓመት በውስኪ ንግድ እንደቆየ ነገረኝ።
"ከ19 ዓመት ጀምሮ እስከ 92 ዓመት የቆየ ውስኪ አለኝ። በስኮትላንድ መጋዘኖች አሉኝ። ደንበኞቼ በ 3,000 ፓውንድ ጀምረው እስከ 50,000 ፓውንድ ኢንቨስት ያደርጋሉ" አለኝ።
"ትልቁ ያከናወንኩት ንግድ 1.4 ሚሊዮን ፓውንድ ነው። እስከ 4 ሚሊዮን ፓውንድ ድረስ ለባንክ ሳናሳውቅ መነገድ እንችላለን" ሲልም ነገረኝ።
የምወክለው ባለሀብት እስከ 1.5 ሚሊዮን ፓውንድ ድረስ ኢንቨስት እንዲያደርግ ክሬግ ጠየቀኝ።
የሰጠኝን የዋጋ ዝርዝር በዘርፉ ላሉ ባለሙያዎች ሳሳይ የተጋነነ ዋጋ እንደሆነ ነገሩኝ። ከትክክለኛው የገበያ ዋጋ አሥር እጥፍ ድረስ የተጋነነ ዋጋ ነበር የሰጠኝ።
"ልናምንህ እንችላለን?" ብዬ ስጠይቀው "አዎ፤ 100% እመኑኝ" ሲል መለሰልኝ።
ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ በጥያቄ ሳፋጥጠው ክሬግ ብሩክስ መሆኑን አመነ። የታሰረው ግን በማጭበርበር ሳይሆን የንግድ አጋሩ ከድቶት እንደሆነ ገለጸልኝ።
ሁለቱ አብረውት የነበሩ ግብረ አበሮችም ስማቸው የተሰጣቸው ድርጅቱን ሲቀላቀሉ መሆኑን አመኑ።
ለስምንት ወራት በቆየ ምርመራዬ በውስኪ ንግድ ውስጥ ያሉ ባለሀብቶችን አሳዛኝ ታሪኮች ሰምቻለሁ።
ወንጀለኞች እንዴት ገንዘብ አጭበርብረው እንደሚወስዱባቸው አይቻለሁ።
አሁን ፖሊሶች በሦስት የስኮች ውስኪ ድርጅቶች ላይ ምርመራ እያደረጉ ነው። በማጭበርበር ነው ምርመራው የተከፈተባው። በሚሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ ባለሀብቶች በእነዚህ ድርጅቶች ላይ አፍስሰዋል።
በዚህ ምርመራ ወቅት የደረስኩበትን አንድ ነገር ልምከራችሁ። በውስኪ ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ የምትፈልጉ ከሆነ መጀመሪያ ምርመራ በማድረግ የቤት ሥራችሁን ጨርሱ።
ሁሉም ሰው እውነተኛ ማንነቱን አይናገርም።