በጎፋ ዞን ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 መድረሱ ተገለጸ

በጎርፍ ጉዳት የደረሰበት አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Gofa Zone Communication

ታትሟል

በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ውስጥ የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ቢያንስ የ21 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የአካባቢው አስተዳደር አስታወቀ።

ሐሙስ ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም. ሌሊት በዞኑ ውስጥ በሚገኘው ኡባ ደብረፀሐይ ወረዳ ዛባ ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ 21 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል።

የዞኑ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሳሁን አባይነህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሐሙስ ሌሊት ከ8፡00 እስከ 10፡00 ሰዓት ድረስ የጣለው ከባድ ዝናብ ነው አደጋውን ያስከተለው።

በጎፋ ዞን አደጋው የደረሰበት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢልቶ ኢፀና አርብ እኩለ ቀን ላይ እንደተናገሩት፣ ከአደጋው በኋላ በተደረገው ፍለጋ በመጀመሪያ ላይ የ15 ሰዎች አስከሬን የተገኘ ሲሆን፣ ከእዚህ መካከልም አምስቱ ህጻናት መሆናቸውን ገልጸው ነበር።

አቶ ካሳሁን እንዳሉት አደጋው የደረሰበት አካባቢ ከተራራ ግርጌ የሚገኝ በመሆኑ ጉዳቱን የከፋ ያደረገው ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ የሟቾች ቁጥር ይጨምራል በሚል ስጋት ፍላጋ ሲደረግ ቆይቷል።

በተደረገው ፍለጋም የተጨማሪ ሰዎች አስከሬን ተገኝቶ በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ከፍ ያለ ሲሆን፣ አንዲት ሴት እስካሁን የደረሱበት እንዳልታወቀም ገልጸዋል።

በአደጋው ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ያጡ ቢያንስ 200 የሚሆኑ በኡባ ደብረፀሐይ ወረዳ ዛባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አባወራዎች ለመፈናቀል መዳረጋቸውን አቶ ካሳሁን አባይነህ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በአደጋው የሞቱ ወይም ጉዳት የደረሰባቸው ተጨማሪ ሰዎችን ለማግኘት የአካባቢው ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች አሁንም ፍለጋ እያካሄዱ መሆናቸውን ም ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጨምረውም “በከተማዋ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕጻናት የነበሩ ሲሆን፣ ከአደጋው በኋላ አስካሁን ያሉበት ባለመታወቁ ይህም የሟቾቹን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አለ” ብለዋል።

አደጋው በደረሰበት የጎፋ ዞን ውስጥ የጣለው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን አለቶችን አንከባሎ ወደ መኖሪያ አካባቢዎች በመውሰዱ በርካታ ቤቶች ከጎርፉ ባሻገር በድንጋዮቹ የመፍረስ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ከባድ ዝናብ እየጣለ ሲሆን፣ ይህም ሊቀጥል እንደሚችል የሚትዮሮሎጂ ባለሙያዎች አሳውቀዋል።

ስለዚህም በከተሞች እና በገጠር አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በከባድ ዝናብ እና እሱን ተከትሎ በሚከሰቱ ጎርፍን የመሳሰሉ አደጋዎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል።

በጎርፍ ጉዳት የደረሰበት አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Gofa Zone Communication