ሩሲያ ለተመድ የቀረበውን የሱዳንን የተኩስ አቁም ሐሳብ ውድቅ ማድረጓ ውዝግብ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሱዳን ተፋላሚ አካላት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ዩናይትድ ኪንግደም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሩስያ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብቷ ውድቅ አድርጋዋለች። እርምጃውን ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ በጽኑ አውግዘውታል።
የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ውሳኔውን “አሳፋሪ” ብለውታል። ሩሲያ ግን ሱዳንን ሳታሳትፍ በሱዳን ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች ስትል ዩናይትድ ኪንግደምን ከሳለች።
ለ19 ወራት የዘለቀው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል ተብሏል። ከ11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
የእርዳታ ሠራተኞች እንዳሉት ከሆነ ግጭቱ በዓለም ላይ እጅግ የከፋውን ሰብአዊ ቀውስ የፈጠረ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ለረሃብ ተጋልጠዋል።
የሱዳን ሰብዓዊ ተሟጋቾች የተባበሩት መንግስታት ለግጭቱ ምላሽ ለመስጠት ቀርፋፋ ሆኗል በሚል ከፍተኛ ትችት ሰንዝረዋል።
ባለፈው አመት በሚያዝያ ወር የጀመረው ጦርነት በአገሪቱ ሠራዊት እና በልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መካከል ለስልጣን በሚደረግ ሽኩቻ ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በሴራሊዮን የቀረበው የሰኞው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ብሔራዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ ውይይት እንዲጀምሩ አሳስቧል።
በተጨማሪም ሠራዊቱ እና አርኤስኤፍ ሲቪሎችን ለመጠበቅ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ስምምነቶችን እንዲያከብሩ ጠይቋል። በተለይም አርኤስኤፍን በመጥቀስ በምዕራባዊው የዳርፉር ክልል እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ሲቪሎችን ለመጠበቅ የተደረሱ ስምምነቶችን እንዲያከበር ጠይቋል።
በተባበሩት መንግስታት የሱዳን ተወካይ በበኩላቸው በረቂቁ ውስጥ የሚፈልጓቸው አንቀጾች አልተካተቱም ብለዋል።
ከሩሲያ ውጭ ሌሎቹ 14ቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት ረቂቁን ደግፈው ድምጽ ቢሰጡም ግን ድምጽን በድምጽ በመሻር ውሳኔው ረቂቁ ሳያልፍ ቀርቷል።
“ይህ የሩስያ ውሳኔ ውርደት ነው። የሩስያን እውነተኛ መልክም ለዓለም በድጋሚ ያሳያል” ሲሉ ላሚ በኒውዮርክ በተደረገው ስብሰባ ተናግረዋል።
"የሩሲያ ተወካይ ስልካቸውን ተጠቅመው በሙሉ ህሊናቸው እንዲመልሱልኝ እጠይቃለሁ። ምን ያህል ሱዳናውያን መገደል አለባቸው? ስንት ተጨማሪ ሴቶች መደፈር አለባቸው? ሩሲያ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት ስንት ተጨማሪ ህፃናት ያለ ምግብ መጥፋት አለባቸው?" ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በበኩላቸው ሩሲያ የሱዳንን አስከፊ ሁኔታ ለመቅረፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እያደናቀፈች መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን ህይወት በመጉዳት የራሷን የፖለቲካ ዓላማ ለማራመድ ሞክራለች" ሲሉ ወቅሰዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩስያ ተወካይ ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ ግን የሱዳን ሉዓላዊነት ችላ እየተባለ ነው ከማለት ባለፈ በእንግሊዝ የተደገፈው የውሳኔ ሃሳብ በሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ነገር ውስጥ “ጣልቃ ለመግባት የተደረገ ሙከራ ነው” ብለዋል።
"ዩናይትድ ኪንግደም አሳፋሪ ናት በሱዳን ቀውስ ውስጥ ቤንዚን የሚያፈስ የውሳኔ ሃሳብን ለመግፋት በመሞከር ምዕራባውያን አገራት በቀድሞ ቅኝ ግዛቶቻቸው ውስጥ በጣም የሚወዱትን አጀንዳ ለመግፋት መሞከር ነው” ሲሉም ከስብሰባው በኋላ ኤክስ ላይ ጽፈዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት ካለቀ በኋላ በተባበሩት መንግስታት የሱዳን አምባሳደር አል ሃሪት ኢድሪስ አል ሀሪዝ መሐመድ አንዳንድ "ቅድመ-ሁኔታዎች" በረቂቁ ውስጥ የሉም ሲሉ ተናግረዋል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ለአርኤስኤፍ የምትሰጠውን ድጋፍ የሚያወግዝ አንቀጽ ሱዳን እንደምትፈልግ ገልጸዋል። የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ግን ይህንን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
አርኤስኤፍ “ሰላማዊ ሰዎችን የማጥፋት ጦርነት ስለሚያካሂድ አሸባሪ” ተብሎ እንዲፈረጅ እንደሚፈልጉም አክለዋል።
ጦር ኃይሉም ሆነ አርኤስኤፍ እስከጦር ወንጀል የሚደርስ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽመዋል በሚል ተከሰዋል።












