በኔዘርላንድ የስደተኞች መጠለያ የሶስት ወር ህጻን ሕይወቱ አለፈ

ታትሟል

በኔዘርላንድስ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞችን በሚያስተናግድ አንድ ማዕከል ውስጥ አንድ የሶስት ወር ህፃን ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ የአገሪቱ የስራ ሃላፊዎች ምርመራ ማካሄድ ጀመሩ።

ሕፃኑ ትላንት እሮብ ማለዳ ላይ በሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ክፍል ተር አፔል ተብሎ በሚጠራው መንደር ውስጥ የድንገተኛ የስደተኞች መጠለያ ሆኖ በሚያገለግል የስፖርት ማዘውተሪያ አዳራሽ ውስጥ ነው የሕጻኑ ህልፈት ሪፖርት የተደረገው።

የሀገሪቱ የጤና እና የወጣቶች ክብካቤ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት በመግለጫው "በሚያሳዝን ሁኔታ የህክምና እርዳታዎች ምንም ውጤት ሳያመጡ ቀርተዋል’’ ሲል ገልጿል።

የሕፃኑ ስም፣ ጾታ እንዲሁም ዜግነት እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።

"ለሕፃኑ ህልፈት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ማናቸውንም አይነት ሁኔታዎች እንመረምራለን’’ ሲል ተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት ገልጿል።

ይህም በማቆያ ጣቢያው የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት ካለ፣ በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ብሎም የስደተኞችን የኑሮ ሁኔታ መመርመርን ይጨምራል።

የሕፃኑ ሕልፈት ዜና የተሰማው ኔዘርላንድ በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀውስ ውስጥ በምትገኝበት ወቅት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በግዜያዊ መጠለያው አግራቢያ በመንገዶች ላይ ተኝተው በሚገኙበት ወቅት መሆኑን የቢቢሲ ዘጋቢ የሆነችው አና ሆሊጋን ከሄግ ገልጻለች።

የቢቢሲ የሄግ የጥገኝነት ጥያቄዎች በበቂ ፍጥነት እየተስተናገዱ ባለመሆናቸው እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ ያለመቻላቸው ለተፈጠረው ችግር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ለጥገኝነት ጠያቂዎች የሚሆን የቦታ እጥረት ተከስቷል።

በርከት ያሉ የኔዘርላንድ የፓርላማ አባላት በዜናው የተሰማቸውን ድንጋጤ ገልጸው ማዕከሉን ከሚመሩ ባለስልጣናት አስቸኳይ ማብራሪያ ጠይቀዋል።