ሊቨርፑል የካራባኦ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊቨርፑል ዌምብሌይ ላይ በተደረገው የካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ቨርጂል ቫን ዳይክ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ቼልሲን በመርታት ዋንጫውን ለመሳም በቃ።
በመደበኛው ሰዓት በጭንቅላት ገጭቶ ያስቆጠራት ኳስ ከጨዋታ ውጭ ተብላ የተሻረችበት ተከላካዩ ተመሳሳይ ጎል በ118ኛው ደቂቃ በማስቆጠር ቡድኑን ለዋንጫ ክብር አብቅቷል።
ዋንጫውን ለ10ኛ ጊዜ ያነሳው ሊቨርፑል እንደ ሞሐመድ ሳላህ፣ ዳርዊን ኑኔዝ፣ አሊሰን፣ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ እና ዲያጎ ጆታ ያሉ ከዋክብቱን በጉዳት ማሰለፍ አልቻለም ነበር።
አማካዩ ሪያን ግራቨነበርችን ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ በጉዳት አጥቶታል።
ቡድኑን በውድድር ዓመቱ መገባደጃ የሚሰናበቱት አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ እየተፎካከሩ ከሚገኙባቸው አራት ውድድሮች አንዱን ዋንጫ ከወዲሁ ለማሳካት በቅተዋል።
ቼልሲዎች በበኩላቸው በዌምብሌይ ያደረጓችውን ስድስት ተከታታይ የፍጻሜ ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ሦስቱን የተሸነፉት በሊቨርፑል ነው።
በዚህ ጨዋታ ቼልሲዎች በርካታ ዕድሎችን አምክነዋል።
የቀያዮቹ ግብ ጠባቂ ቻኦሚን ኬለር የሰማያዊዎቹን በርካታ ድንቅ ሙከራዎችን በማክሸፍ ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ኮል ፓልመርን ሙከራ ሲያድን ራሂም ስተርሊንግ ያስቆጠራት ጎል ደግሞ ከጨዋታ ውጭ ተብላ ተሽራለች።
የቀያዮቹ አጥቂ ኮዲ ጋክፖ የሞከራት ኳስ ደግሞ በግቡ አግዳሚ ተመልሳለች።
በርካታ ሙከራዎች በነበሩበት ሁለተኛው አጋማሽ ቫንዳይክ በጭንቅላት ያስቆጠራት ጎል አማካዩ ዋታሩ ኤንዶ ከጨዋታ ውጭ ሆኖ የቸልሲን ተከላካይ እንቅስቃሴ በመግታቱ በአጨቃጫቂ ሁኔታ ተሰርዛለች።
ኮኖር ጋላገር ሰማያዊዎቹን ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል ሙከራ ቢያደርግም ኳሷ የግቡን ቋሚ ገጭታ ተመልሳለች።
ሁለቱ ቡድኖች በዚህ መልኩ መደበኛው ሰዓት አጠናቀው ከተጨማሪው ሰዓት በኋላ ወደ መለያ ምት ሊያመሩ ነው ሲባል ቫንዳይክ በ 118ኛው ደቂቃ የአሸናፊነት ጎሏን አስቆጥሯል።
በርካታ ከዋክብትን በጉዳት ማሰለፍ ያልቻለው ሊቨርፑል በምትኩ ታዳጊዎችን አሰልፎ የዋንጫ ባለቤት በመሆኑ ሙገሳ እየጎረፈለት ነው።
በርካታ ዋንጫዎችን በቀያዮቹ ያጣው የፖቸቲኖ ቡድን በጉዳት የሳሳውን ሊቨርፑልን በማሸነፍ ለመበቀል የነበረውን ዕድል አምክኗል።
ፖቸቲኖም በእንግሊዝ ምድር የመጀመሪያውን ዋንጫ ለማንሳት ነበራቸው ህልም ከሽፏል።
ቼልሲዎች በመደበኛው ሰዓት ያገኟቸውን ዕድሎች ካለመጠቀማቸውም በላይ በተጨማሪው ሰዓት በሊቨርፑል ተበልጠዋል።
ቼልሲዎች ዋንጫውን ቢያነሱ በአውሮፓ መድረክ የመወዳደር ዕድልን ከመፍጠሩም ባለፈ በደካማው የውድድር ዘመን የሚደርስባቸውን ትችት የሚቀንስ ይሆን ነበር።












