በዋሽንግተን የእስራኤል ኤምባሲ ደጃፍ እራሱን በእሳት ያቃጠለው የአሜሪካ የአየር ኃይል አባል ሕይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ከሚገኘው የአስራኤል ኤምባሲ ፊት ለፊት እራሱን በእሳት ያቃጠለው የአሜሪካ የአየር ኃይል አባል በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ አለፈ።
ከቴክሳስ ሳን አንቶኒዮ የመጣው ግለሰብ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ስሙም አረን ቡሽኔል እንደሚባል ፖሊስ አስታውቋል።
የአየር ኃይል አባሉ እሁድ ከሰዓት በኋላ እራሱን በእሳት እንዳያያዘ በአካባቢው በነበሩ የደኅንነት ሠራተኞች እሳቱ ጠፍቶለት ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።
ግለሰቡ እራሱን በእሳት ከማቃጠሉ በፊት “ ከአሁን በኋላ የዘር ማጥፋት ተባባሪ አልሆንም” እንዲሁም እየተቃጠለ “ነጻ ፍልስጤም” ሲልም ተደምጧል።
በትዊች የማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋራ ቪዲዮም የአሜሪካ አየር ኃይል አባል መሆኑን እንዲሁም ማንነቱንም ከተናገረ በኋላ ነው ራሱን ያቃጠለው።
የአሜሪካ የደኅንነት አገልግሎት መኮንኖች ከግለሰቡ ላይ እሳቱን ማጥፋታቸው ያስታወቁ ሲሆን፣ ሕይወቱ በአስጊ ደረጃ ላይ መሆኑም ተነግሮ ነበር።
በእሳቱ የተነሳ ግለሰቡ ከባድ እና ለሕይወት አስጊ የሆኑ ጉዳቶች አጋጥመውት ወደ ሆስፒታል መወሰዱን የከተማው የእሳት አደጋ መከላከያ አረጋግጧል።
የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ቃል አቀባይን ጠቅሰው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ግለሰቡ የአየር ኃይሉ ባልደረባ ነበር።
የዋሽንግተን ፖሊስ ዲፓርትመንት ከደኅንነት አገልግሎት እና ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ምርመራ እያደረገ ነበር።
ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ድርጊቱ የተፈፀመው በርካታ ኤምባሲዎች በሚገኙበት አካባቢ መሆኑን ጠቅሶ የአሜሪካ የደኅንነት አገልግሎትን እንዲያግዙ ሠራተኞቻቸውን መላካቸውን አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም አንድ “አዋቂ ወንድ” ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን፣ “በአስጊ ሁኔታ ውስጥ” እንዳለ አክሏል።
ከግለሰቡ ጋር ሊገናኝ ይችላል የተባለ አጠራጣሪ መኪና ላይ በተፈጠረ ስጋት የተነሳ የቦምብ ማስወገጃ ሠራተኞች እንዲመረምሩት ተደርጓል።
በኋላም ምንም አደገኛ ቁሳቁሶች እንዳልተገኙ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑ ተረጋግጧል።
በድርጊቱ የኤምባሲው ሠራተኞች ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የኤምባሲው ቃል አቀባይ ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ግለሰቡ በኤምባሲው ሠራተኞች ዘንድ እንደማይታወቅ አመልክቷል።
ይህ ግለሰብ በአሜሪካ በሚገኝ የእስራኤል ቆንስላ ፊት ራሱን ሲያቃጥል የመጀመሪያው አይደለም።
በታኅሣሥ ወር አንድ ተቃዋሚ በዩናይትድ ስቴትስ ጆርጂያ ግዛት በሚገኘው የእስራኤል ቆንስላ ፊት ለፊት በተመሳሳይ ራሱን አቃጥሎ ነበር።
ፖሊስ በወቅቱ እንዳስታወቀው ሰልፈኛው ቤንዚን የተጠቀመ ሲሆን የፍልስጤም ባንዲራም በቦታው ተገኝቷል።
እነዚህ ክስተቶች እስራኤል በሐማስ የተፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ ላይ እያካሄደችው ያለውን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት በመቃወም መሆኑ ተገልጿል።












