ኦዲንጋ የኬንያ ምርጫ ውጤትን ለማሰረዝ በፍርድ ቤት ክስ መሰረቱ

ታትሟል

ራይላ ኦዲንጋ በቅርቡ የተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት በመቃወም ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ከሁለት ሳምንታት በፊት ተካሂዶ በነበረው ምርጫ በጠባብ የውጤት ልዩነት በወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መሸነፋቸው ታውጆ ነበር።

ይሁን እንጂ ተቃዋሚ ፖለቲከኛው እና በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚደገፉት ራይላ ኦዲንጋ፤ የምርጫ ውጤቱ ውድቅ እና ተቀባይነት የሌለው ነው ካሉ በኋላ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ገልጸው ነበር።

የራይላ ኦዲንጋ ጥምር ፓርቲ የሆነው አዚሚዮ የሕግ ቡድን የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ውድቅ ለማስደረግ ለፍርድ ቤት አቤቱታውን ማቅረቡን አስታውቋል።

የኬንያ ገለልተኛ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ከተሰጠው አጠቃላይ ድምጽ ዊሊያም ሩቶ 50.5 በመቶ እንዲሁም ራይላ ኦዲንጋ 48.8 በመቶ ማግኘታቸውን በመጥቀስ ዊሊያም ሩቶን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሲል ባለፈው ሳምንት አውጆ ነበር።

በአገሪቱ ሕግ መሠረት የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ተቃውሞ ያለው አካል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታውን ማሰማት አለበት።

በዚህም መሠረት ነው ኦዲንጋ ውጤቱን አልቀበለውም ያሉትም ምርጫ በተመለከተ በታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች አማካይነት አቤቱታ ያቀረቡት።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዋፉላ ቼቡካቲ ዊሊያም ሩቶን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ብለው ያውጁ እንጂ ሁሉም የኮሚሽኑ አባላት በምርጫ ውጤቱ አልተስማሙም።

የኬንያን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ያስፈጸመው ኮሚሽን 7 ኮሚሽነሮች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አራቱ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤቱ አለመስማማታቸውን በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር።

ኮሚሽነሮቹ የምርጫው አካሄድ “ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ ለውጤቱ ኃላፊነት መውሰድ አንችልም”  ማለታቸው ለራይላ ኦዲንጋ የፍርድ ቤት ክርክር ኃይል የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል።

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ የቀረበውን ክስ መርምሮ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ብይን መስጠት አለበት። ፍርድ ቤቱ ከአምስት ዓመት በፊት ተካሂዶ የነበረውን የምርጫ ውጤት ውድቅ ካደረገ በኋላ ኬንያ ዳግም ምርጫ ማካሄድ ግድ ብሏት ነበር።

እአአ 2017 ላይ በተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሁን ሥልጣን ላይ ባሉት ኡሁሩ ኬንያታ ተሸንፈው የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ውስደው የምርጫ ውጤቱን ‘ውድቅ እና ተቀባይነት የሌለው’ አስብለው ነበር።

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በ60 ቀናት ውስጥ በተደረገው ዳግም ምርጫ ኦዲንጋ እራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ኡሁሩ ኬንያታ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ማሸነፍ ችለው ነበር።