በኬንያ በደረሰ የከባድ መኪና አደጋ ቢያንስ 48 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በኬንያ እንቅስቃሴ በሚበዛበት መስቀለኛ መንገድ ላይ በደረሰ በአንድ የትራፊክ አደጋ ቢያንስ 48 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ እና የዐይን እማኞች ገለጹ።

አደጋው የተከሰተው ኮንቴኔር የጫነ ከባድ ተሽከርካሪ በምዕራባዊቷ ከተማ ኬሪቾ አቅራቢያ በሚገኝ ሎንዲያኒ መስቀለኛ መንገድ ላይ ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ እንደሆነ የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፖሊስ አዛዡ ጄፍሪ ማዬክ እንደተናገሩት በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች 30 ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የተጎጂዎች ቁጥርም ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል የፖሊስ አዛዡ ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪም አንድ ወይም ሁለት ሰዎች አሁንም በተገለበጠው ተሽከርካሪ ሥር ሳይሆኑ እንዳልቀሩም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የፈረንሳዩ የዜና ወኪል (ኤኤፍፒ)፣ ቶም ምቦያ ኦደሮ የተባሉ ሌላ የአካባቢው የፖሊስ መኮንን ጠቅሶ እንደዘገበው ወደ ኬሪቾ ሲጓዝ የነበረው ከባድ ተሽከርካሪ ፍጥነቱን መቆጣጠር አቅቶት ስምንት መኪኖችን፣ በርካታ ሞተርሳይክሎችን፣ በመንገድ ዳር የነበሩ ሰዎችን፣ በጎዳና ላይ እቃ ሲሸጡ የነበሩ እንዲሁም በሌላ ሥራ ላይ የነበሩ ሰዎችን ገጭቷል።

የዐይን እማኞችም ተሽከርካሪው በመንገዱ ላይ ተበላሽቶ የቆመውን አውቶብስ ለማለፍ ሲሞክር ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ አደጋው መከሰቱን ለኬንያ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው የወደፊት አገር ተረካቢ ወጣቶች እና በዕለታዊ ሥራቸው ላይ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን ሲሰሙ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

“በተለይ በዝናብ ወቅት የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች በጉዞ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም” ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አሳስበዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተዘዋወሩ ምስሎች ቀይ የእቃ ማጓጓዣ ኮንቴነር የጫነ ተሽከርካሪ በመንገዱ ዳር በጎኑ ወድቆ አሳይተዋል።

የከተማዋ አስተዳዳሪ ዶክተር ኤሪክ ሙታይ አደጋው የተከሰተበትን ዕለት ለኬሪቾ 'ጥቁር ቀን' ሲሉ ገልጸውታል።

አስተዳዳሪው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ከተሽከርካሪው ምስል ጋር “ልቤ ክፉኛ ተሰብሯል” የሚል ጽሑፍ አጋርተዋል።

ዶክተር ሙታይ ጨምረውም በአደጋው ቦታ የድንገተኛ ነፍስ አድን አገልግሎት ሠራተኞች ተሰማርተዋል ብለዋል።

ሆኖም በአካባቢው እየዘነበ ያለው ዝናብ የነፍስ አድን ሥራውን እንዳስተጓጎለው የተገለጸ ሲሆን፣ ዝናቡ ለአደጋው አንደኛው መንስኤ ስለመሆኑ ግን ግልጽ አይደለም።

ከከተሞች ውጪ ያሉ መንገዶች ጠባብ በመሆናቸው የመንገድ ላይ አደጋ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ የተለመደ ክስተት ነው።

ባለፈው ዓመት በማዕከላዊ ኬንያ አንድ አውቶብስ ድልድይ ጥሶ ኒቲ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ 34 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት በድረ ገጹ ላይ እንዳስታወቀው አህጉሪቷ በዓለም ከፍተኛ የትራፊክ ሞት መጠን ተመዝግቦባታል።