ሩሲያ የክተት ጥሪው የማይመለከታቸውን የሥራ መስኮች ይፋ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩክሬንን ጦርነት ለማፋፋም በሚል ለዜጎቿ ጥሪ ያደረገችው ሩሲያ ምልመላው የማይመለከታቸውን ዘርፎች ይፋ አድርጋለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ክተቱ ሁሉንም ዜጎች የሚመለከት አይደለም።
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የባንክ ባለሙያዎች፣ እና ለብሔራዊ አገልግሎት የሚሠሩ ጋዜጠኞች ክተቱ ከማያካትታቸው መሀል ተደርገዋል።
ይህ መግለጫ የወጣው በርካታ ሩሲያዊያን ወደ ጎረቤት አገር ለመሸሽ ሻንጣቸውን መሸከፍ መጀመራቸው ሳይሆን አይቀርም።
ፑቲን ለተጠባባቂ 300ሺህ ወታደሮች ጥሪ ካደረጉ ወዲህ በርካታ ሩሲያዊያን ባለ በሌለ ፍጥነት አገር ለቀው ለመሰደድ ሙከራ እያደረጉ ነው።
በተለይ በጎረቤት ጆርጂያ በኩል ከፍተኛ የመኪና ሰልፎች ተስተውለዋል።
ቱርክና ዱባይ የአውሮፕላን ትኬት የሚቆርጡ ሩሲያዊያን ቁጥር አሻቅቧል።
መከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ዐርብ ጥሪው የማይመለከታቸውን ከዘረዘረ በኋላ ሌሎች ሠራተኞች ግን ስም ዝርዝራቸው ለሚመለከታቸው ቢሮዎች እንዲላክ አሳስቧል።
በፋይናንስ ሲስተምና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሉ ከፍተኛ ባለሙያዎችም ጥሪው ከማይመለከታቸው መካከል ናቸው።
አንዳንድ ታዛቢዎች መመሪያው ሆን ተብሎ ግልጽነት ጎድሎታል ብለዋል።
ጥሪው ማንን ይመለከታል፣ ማንን አይመለከትም የሚለው ብዥታ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ይላሉ እነዚህ ታዛቢዎች።
ምክንያቱም የአካባቢ ባለሥልጣናት ያሻቸውን እንዲያደርጉና የሚሸሹ ዜጎችንም ለመቀነስ ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ይጠረጥራሉ።
በሩሲያ ከሚታተሙ ነጻ ጋዜጦች አንዱ ኖቫያ ጋዜታ አንድ በስም ያልተጠቀሱ ባለሥልጣንን ምንጭ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ የሚፈለገው የሠራዊት ቁጥር ፑቲን እንዳሉት 300ሺህ ሳይሆን አንድ ሚሊዮን ነው።
ሌላ ባለሥልጣን በበኩላቸው በክሬምሊን አዲስ ምልመላ የማድረግ ሐሳብ ጭራሽ እንዳልተመከረበት ተናግረዋል።
በሩሲያ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ አይመለከታቸውም የተባሉ ወጣቶች ጭምር የክተት ጥሪ ደርሷቸዋል።
የሩሲያ ዕለታዊ ጋዜጣ ኮሜርሳንት እንደዘገበው በሳይቤሪያ ክልል ቀደም ብሎ በጤና ምክንያት ከወታደር ቤት ነጻ የተባሉ በድጋሚ ሪፖርት እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል።
የዘመቻ ጥሪን ተከትሎ በአብዛኛው የሩሲያ ከተሞች ከአገር ለመውጣት ሩጫ ታይቷል።
ይህ የወታደር ክተት ጥሪ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በመጠኑ ግዙፍ ነው ተብሏል።
ሩሲያና ጆርጂያን በሚያዋስነው ድንበር የመኪናው ሰልፍ በኪሎ ሜትሮች ሆኗል።
ከ12 ሰዓት በላይ ሰልፍ ላይ ነበርን ያሉ ሩሲያዊያን ለቢቢሲ የሁኔታውን አስከፊነት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዳንዶች የመኪናውን ሰልፍ ለመቅደም ብስክሌት ለመጠቀም ሞክረዋል።
አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሩሲያዊ የወታደር ምልመላው ቀደም ብሎ የነበረ ቢሆንም ፑቲን ቁጥሩን ይፋ ካደረጉ ወዲህ ግን ፍርሃት መንገሡን አብራርቷል።
ሌላ ሩሲያዊ ተማሪ በበኩሉ የፑቲንን ንግግር ተከትሎ "ራሺያዊያን ዐይናቸውን ከፍተዋል፤ ልጆቻቸውን የት መደበቅ እንዳለባቸው እያሰቡ ነው" ሲል ለቢቢሲ አስተያየቱን ሰጥቷል።
"አሁን ሰዎች ምን እየሆነ እንዳለ መረዳት ጀምረዋል፤ ምክንያቱም ችግሩ እነሱም ላይ መጣ።"
ሌላ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ለቢቢሲ ጦርነቱን እንደማይደግፈው ተናግሮ ነገር ግን ይህን ተቃውሞውን በአደባባይ መናገር እንደሚፈራ ገልጧል።
"ሕይወቴን አደጋ ላይ መጣል አልፈልግም፤ የቤተሰቤን ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አልሻም፤ ማጎሪያ ውስጥ እንድታሰርም አልፈልግም ይላል።
"ስለዚህም ሸንገን ቪዛ ለማግኘት ሞከርኩ፤ ተሳካልኝ።"
ሩሲያዊያን በብዛት አገር ለመልቀቅ እየተጠቀሙበት ያሉት የጆርጂያ ድንበር ያለ ቪዛ መግባት ስለሚቻል ነው።
ከሩሲያ ጋር 1ሺህ 300 ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራው ፊንላንድ ያለ ቪዛ ሩሲያዊያንን አታስተናግድም።
ከዚህ ሌላ በአየር በረራ ወደ ኢስታንቡል፣ ቤልግሬድ እና ዱባይ የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ የማይቀመስ ሆኗል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሐሙስ ዕለት ምልመላውን ሸሽተው የሚሰደዱ ሩሲያዊያንን ለመቀበል አገራቸው ፍቃደኛ መሆኗን ጠቆም አድርገዋል።
ይሁንና እንደ ሉቲኒያ፣ ላቲቪያ፥ ኢስቶኒያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ያሉ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ለሚሰደዱ ሩሲያዊያን ጥገኝነት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
የክተት ጥሪው በዋና ዋና የሩሲያ ከተሞች ተቃውሞን ጋብዟል።
በሞስኮ እና በቅዱስ ፒተርስበርግ ማክሰኞ ዕለት በተደረገ ተቃውሞ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ታስረዋል።












