የአውሮፓ ኅብረት የፑቲንን ‘ኒውክሊየር እጠቀማለሁ’ ማስፈራሪያ ችላ እንዳይለው ተጠየቀ

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬኑ ጦርነት የኒውክሊየር መሣሪያን እንደሚጠቀሙ ማስፈራራታቸውን የአውሮፓ ኅብረት በቀላሉ እንዳይመለከተው ተጠየቀ።
የፑቲንን ማስፈራሪያ የአውሮፓ ኅብረት በጥንቃቄ እንዲመለከተው የጠየቁት የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ናቸው።
ፑቲን የኒውክሊየር መሣሪያ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ሲያስፈራሩ “አያደርጉትም ” ብሎ ችላ ማለት እንደማይባ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ሩሲያ በአሁኑ ወቅት አራት የዩክሬን ክልሎችን ወደ ግዛቷ ለማጠቃለል እንቅስቃሴ እያደረገች ነው።
ባለፉት ሳምንታት የዩክሬን ኃይሎች በመልሶ ማጥቃት ተይዘውባቸው የነበሩ ግዛቶቻቸውን ከሩሲያ ማስመለሳቸው አይዘነጋም።
“የሩሲያ ኃይል እየተገፋ መምጣቱ ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋል። ፑቲን በምላሹ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያን ለመጠቀም ማስፈራራታቸው አስከፊ ነው” ብለዋል ጆሴፍ ቦሬል።
የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣኑ እንደሚሉት ለዩክሬን ጦርነት “ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ” ያስፈልጋል።
“የዩክሬንን ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ መፍትሔ ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን ጦርነቱ ቢያልቅም ሰላም አናገኝም። ሌላ ጦርነት ሊነሳም ይችላል” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዘንድሮው ጠቅላላ ጉባዔ ዋነኛ አጀንዳ ዩክሬን ሆናለች።
ፖለቲከኞች እንዲሁም መደበኛ ዜጎችም ጦርነቱ መቼ እንደሚያበቃ እየጠየቁ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ለመብራት መክፈል አልቻልኩም። ይህንን ጦርነት አቁሙት” የሚሏቸው እንዳሉ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ሩሲያ ትርክቱን በሚያመቻት መንገድ በማስኬድ እየደረሰ ላለው ቀውስ ተጠያቂ የምዕራባውያን ማዕቀብ ነው እንደምትልና በተቃራኒው የአውሮፓ ኅብረት የጦርነቱን ትርክት ለመቆጣጠር እየታገለ እንደሆነም አክለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን እያደረገ ያለው የጦር መሣሪያ ድጋፍ እየቀነሰ ነው የሚለውን አስተባብለዋል። ለዩክሬን የሚደረገው መሣሪያ ድጋፍ እንደሚቀጥልና ፑቲን እንዲሁም አጋሮቻቸው ላይ የሚጣለው ማዕቀብ እንደማይገታም ተናግረዋል።
ፑቲን የኒውክሌር መሣሪያ እጠቀማለሁ ማለታቸው አሳሳቢ መሆኑን አስምረውበታል።
ጆሴፍ ቦሬል በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መናሩ እንደሚያሰጋም ጠቅሰዋል።
“የጋዝ ዋጋ በመወደዱ ምክንያት መሥራት አልቻልንም ብለው የሚነግሩኝ የአገሬ ልጆች አሉ። ተመሳሳይ እሮሮ ከአፍሪካ፣ ከደቡብ አሜሪካ እና ከደቡብ ምሥራቅ እስያም ሰምቻለሁ። ይህ ጦርነት እያሳደረ ያለው ጫና ከፍተኛ ነው” ብለዋል።
ፑቲን በድርድር ላይ የተመሠረተ መፍትሔ እንዲመጣ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
“ወደ ሞስኮ ከፑቲን ጋር ለመነጋገር የሄዱ በአጠቃላይ የሚናገሩት ነገር ተመሳሳይ ነው። ይህም ፑቲን ‘ወታደራዊ ግቤን ሳላሳካ ውጊያ አላቆምም’ ማለታቸውን ነው። ይሄ አስጊ ነው። እናም ዩክሬንን በመደገፍ መቀጠል አለብን” ብለዋል የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣኑ ጆሴፍ ቦሬል።












