ሩሲያ ገንዘብ ሳታጣ ከምዕተ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ዕዳዋን ለመክፈል ተቸገረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ ምናልባትም ከመቶ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ዕዳ ለመክፈል ፈተና ገጥሟታል።
ትናንት እሑድ መክፈል የነበረባትን 100 ሚሊዮን ዶላር የዕዳ ወለድ ሳትከፍል ቀርታለች።
ይህም የሆነው በገንዘብ ዕጦት ሳይሆን በምዕራብ አገራት ማዕቀብ የተነሳ የክፍያ ሒደቱ ውስብስብና አስቸጋሪ ስለሆነ ነው።
ሩሲያ ይህን የዕዳ መክፈያ ቀነ ቀጠሮ ማሳለፏ ለገዘፈ ስምና ዝናዋ መልካም አይደለም ተብሏል።
የሩሲያ የገንዘብ ሚኒስትር ነገሩን “ቧልት” ሲሉ ተሳልቀውበታል።
ሩሲያ ለመጨረሻ ጊዜ የዕዳ መክፈል ሳትችል ቀነ ቀጠሮን ያሳለፈችው እንደ አውሮፓውያኑ በ1918 ዓ.ም በቦልሸቪክ አብዮት ጊዜ ነበር።
ያን ጊዜ ወደ ሥልጣን መጥቶ የነበረው የኮሚኒስቱ መሪ ቭላድሚር ሌኒን የሩሲያ ሥርወ መንግሥትን ዕዳ የመክፈል ዕዳ የለብኝም በማለቱ ነበር ሳይከፈል የቀረው።
ከዚያ ወዲያ በቦሪስ የልሲን ዘመን የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል ቀውስ ተከስቶ በአገር ውስጥ ዕዳ ለመክፈል ፈተና ሆኖ የነበረ ሲሆን፣ የውጭ ዕዳ ግን በአግባቡ ቀን ሳይዛነፍ ተከፍሎ ነበር።
አሁን ሩሲያ በዋናነት ለመክፈል የተቸገረችው በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ለማስተላለፍ የተጣለባት ማዕቀብ አላፈናፍን ስላላት ነው።
ለጊዜው 40 ቢሊዮን ዶላር ለዕዳ መክፈያ የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ግማሹ በውጭ ባንኮች ነበር የተቀመጠው።
ይሁንና ማዕቀቡ የገንዘብ ዝውውሩን አስቸጋሪ አድርጎታል።
ሩሲያ በግንቦት የዛሬ ወር አካባቢ 100 ሚሊዮን ዶላር ወለድ መክፈል ይጠበቅባት ነበር።
ይህን ክፍያ በወቅቱ ለመዝጋት ገንዘብ ወደ ዩሮክሊር ባንክ ልካ ነበር።
ዩሮክሊር ባንክ ሩሲያ የተበደረችውን ገንዘብ ለባለሀብቶችና ለሚገባቸው ባንኮች የሚያሰራጭ ባንክ ነው።
ይሁንና ብሉምበርግ እንዳለው ዩሮክሊር ባንክ ይህን ገንዘብ ለሚገባቸው ለማስተላለፍ ማዕቀቡ አንቆ ይዞታል።
ከግንቦት እስከ ትናንት ድረስ ለአበዳሪዎች ባለመድረሱ ሩሲያ ዕዳ እንዳልከፈለች ተቆጥሮባታል።
ዩሮክሊር ባንክ በጉዳዩ ተጠይቆ ያለው ነገር ባይኖርም፣ የአውሮፓ ኅብረት የሚጥላቸውን ማዕቀቦች ደንብ እንደሚከተል ግን አስታውቋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀቡ ሩሲያ ዕዳ እንድትከፍል ብቻ በሚያስችል መልኩ ያሻሽለዋል በሚል ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም አሜሪካ ይህን ሳትፈቅድ ቀርታለች።
አሁን ክሬምሊን አማራጭ በማጣቱ አበዳሪዎቼ ከእንግዲህ ዕዳችሁን የምመልሰው በሩብል ብቻ ነው ሲል አስታውቋል።
ይሁንና የሩሲያ መንግሥት ብድር ሲወስድ ለመክፈል የተሰማማው በዩሮና በዶላር ብቻ ነበር።
ይህም በመሆኑ በሩብል ለመክፈል ተገድጃለሁ ማለት ስምምነትን የሚጥስ ሆኖ ተገኝቷል።
የሩሲያ የገንዘብ ሚኒስትር እንደተናገሩት ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ከሩሲያ ገንዘብ እንዳይቀበሉ በመደረጉ እንዲሁም በማዕቀቡ የተነሳ ገንዘብ ማስተላለፍ አስቸጋሪ በመሆኑ አገራቸው ዕዳ መክፈል ተቸግራለች።
“መቼስ ሁሉም ሰው ዕዳ መክፈል የተቸገርነው አቅቶን እንዳልሆነ ያውቃል” ብለዋል።
ሩሲያ ነዳጅ ወደ ውጭ በመሸጥ ብቻ በቀን ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታጋብሳለች።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ሩሲያ ከዚህ በኋላ ከውጭ አበዳሪዎች ገንዘብ የመበደር ዕቅድ እንደሌላት ተናግረዋል።












