ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ የመንገደኞች አውሮፕላን የፊት ጎማ ሳይኖረው በሰው ላይ ጉዳት ሳይደርስ አረፈ
ከአንድ መቶ በላይ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው የአሜሪካው አየር መንገድ ዴልታ የመንገደኞች አውሮፕላን ለማረፍ የሚያገለግለው የፊተኛ የጎማው ክፍል ሳይኖረው ምንም ጉዳት ሳይደርስ ለማረፍ ቻለ።
ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ የፊት ጎማ ያልነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን፣ በአሜሪካ ኖርዝ ካሮላይና ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሻርለት-ዳግላስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ረቡዕ ማረፉን አየር መንገዱ አሳውቋል።
አውሮፕላኑ 96 መንገደኞችን እና ተጨማሪ የበረራ ሠራተኞችን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ በሚያርፍበት ጊዜ በማንም ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱም ተገልጿል።
ይህ የአውሮፕላኑ የፊት ጎማ ክፍል አንድ አውሮፕላን በሚነሳበት፣ በሚያርፍበት፣ በሚንደረደርበት እና በሚቆምበት ጊዜ ጉዳት እንዳይደርስበት የሚደግፍ ዋነኛ ክፍል ነው።
የዴልታ አውሮፕላን የሆነው ቦይን 717 አውሮፕላን በረራውን አጠናቆ ለማረፍ አስፈላጊ የሆነው የፊተኛ ጎማው ሳይኖር ካረፈ በኋላ ባለበት እንዲቆም ተደርጎ፣ ሁሉም ተጓዦች እንዲወርዱ ተደርጓል።
አውሮፕላኑ በአጠቃላይ 104 ሰዎችን ይዞ ረቡዕ ዕለት ከአትላንታ በመነሳት ነበር ወደ ሻርለት-ዳግላስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የደረሰው።
ዴልታ አየር መንገድ ክስተቱን በማስመልከት ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ፣ ሁኔታውን “ያልተለመደ ክስተት” በማለት የአየር መንገዱ ሠራተኞች ባላቸው መጠነ ሰፊ ሥልጠና አማካይነት “በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ አውሮፕላኑን ማሳረፍ ችለዋል” ብሏል።
“በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ትኩረታችን የመንገደኞችን ሻንጣዎች ከአውሮፕላኑ ማውጣትን እና ወደ ቀጣይ የጉዞ መዳረሻቸው እንዲጓዙ ማድረግን ጨምሮ የደንበኞቻችንን ፍላጎት ማሟላት ነው” ብሏል ዴልታ አየር መንገድ።
የአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ላይ በቀረበ ከአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል የተገኘ የድምጽ ቅጂ ላይ፣ እክል ያጋጠመው በረራ 1092 የተባለው አውሮፕላን አብራሪ የፊት ጎማው ለማረፍ አስተማማኝ አለመሆኑን የሚገልጽ መልዕክት ሲያስተላልፍ ተሰምቷል።
ፓይለቱ ጨምሮም በአውሮፕላኑ ውስጥ 104 ሰዎች እንዳሉ እንዲሁም ለ50 ደቂቃ አየር ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ነዳጅ እንደያዘ እና በአደጋ ጊዜ ሁኔታ ለማረፍ እንደሚገደድ ለመቆጣጠሪያ ማዕከሉ አሳውቋል።
አውሮፕላኑ ያረፈበት ሻርለት-ዳግላስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በትዊተር ላይ ባሰራጨው መግለጫ፣ የዴልታ አውሮፕላን ባጋጠመው “በሜካኒካል ችግር ምክንያት” ያለበት የመንደርደሪያ ሜዳ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ገልጿል።
አስካሁን የአውሮፕላኑ የፊተኛ የጎማ ክፍል ምን እንዳጋጠመው እና በምን ምክንያት በቦታው ላይገኝ እንደቻለ የተገለጸ ነገር የለም።