ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመሸጥ ጨረታ አወጣ
የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን በጨረታ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች መሸጥ እንደሚፈልግ አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው የጨረታ ጥሪ ላይ እንደተመለከተው የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች በስኳር ፋብሪካዎቹ ግዢ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።
በመንግሥት ይዞታ ስር የሚገኙት እና ለሽያጭ የቀረቡት ስኳር ፋብሪካዎች፡ ኦሞ ኩራዝ 1፣ 2፣ 3 እና 5፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰመ፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ ናቸው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ጨረታውን ያወጣው በዘርፉ ተወዳዳሪነትን ከፍ ለማድረግ እና የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት ያለመ መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ፍጆታን ለመሸፈን በከፍታኛ የውጭ ምንዛሪ ስኳር ከውጪ አገራት እንደምታስገባ ያመላከተው የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ስምንቱ ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ መሸጋገራቸው ተወዳዳሪነትን እና ምርትን ይጨምራል ብሏል።
የስኳር ምርት ዘርፍ ማደግ የስኳር ሸንኮራ አገዳ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላሉ የማኅብረሰብ ክፍሎች ሕይወት እና ገቢ መሸሻል ያስገኛሉም ተብሏል።
የአገር ውስጥ የውጪ ባለሃብቶች ወደ ስኳር ዘርፉ መግባታቸው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ስኳር ከማምረት በተጨማሪ የተለያዩ የስኳር አይነቶችን ወደ ውጪ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ብሏል የገንዘብ ሚኒስቴር።
የገንዘብ ሚኒስቴር ለጨረታ ያቀረብኳቸው የስኳር ፋብሪካዎች በቅርቡ የተገነቡ እና የሚገኙባቸው ስፍራዎችም ለሸንኮራ አገዳ ምርት ምቹ፣ ከፍተኛ የውሃ ሃብት ያለበት፣ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው መሆናቸውን ገልጿል።
ይህንን ፋብሪካዎቹን ወደ ግል የማዞር ሂደት ኧርነስት ኤንድ ያንግ ያተባለውን አማካሪ ተቋም በአማካሪነት ሂደቱ ግልጽ እና የተሳካ እንዲሆን ሥራውን እንደሚያካናውን ተገልጿል።
የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው የአገር ውስጥ፣ ዓለም አቀፍ ወይም ጥምር ተቋማት ፍላጎታቸውን የሚገልጽ ሰንድ እንዲያቀርቡ የገንዘብ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
ከአራት ዓመት በፊት የውቅቱ ገዢ ፓርቲ የነበረው ኢህአዴግ ግምገማ አድርጎ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል፣ ለአስርታት በመንግሥት ብቸኛ ቁጥጥር ስር የነበሩ እና በግንባታ ላይ ያሉ ማምረቻ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ባለቤትነት እንዲዘዋወሩ መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ ተወስኖ ነበር።
ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል የማዞር ሃሰብ እንዲሰረዝ ሲደረግ፣ ይህ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል የማዞሩ ጥሪ ውሳኔው ከተላለፈ ከዓመታት በኋላ የቀረበ ነው።