ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስትል፡ ዋንጫ የጠማቸው ቡድኖች የሚያደርጉት ፍልሚያ
ቀንና ሰዓት፡ እሑድ የካቲት 18፤ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1፡30
ቦታ፡ ለንደን የሚገኘው ግዙፉ ዌምብሊ ስታድዬም
በካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ ማንቸስተር ዩናይትድና ኒውካስትል ይገናኛሉ።
የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ኖቲንግሃም ፎረስትን በሁለት ዙር ፍልሚያ 5-0 ረትቶ ነው ለፍፃሜ የደረሰው። የኤዲ ሃው ኒውካስትል ደግሞ ሳውዝሃምፕተንን 3-1 በመርታት ከ24 ዓመታት በኋላ ለፍፃሜ ደርሷል።
ቀያዮቹ ሰይጣኖች ከካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ ባለፈ፣ለ በፕሪሚዬር ሊጉ፣ በኤፍ ኤ ዋንጫና በአውሮፓ ሊግ እየተፋለሙ ይገኛሉ።
ማንቸስተር ዩናይትድ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ያነሳው በፈረንጆቹ 2016/17 የውድድር ዘመን ሲሆን ጆዜ ሞውሪንሆ የአውሮፓ ሊግና ኢኤፍኤል ዋንጫን ለቡድን አስገኝተዋል።
በፈረንጆቹ 199 የኤፍኤ ዋንጫ በማንቸስተር ዩናይትድ የተሸነፉት ኒወካስትል ዋንጫ ካነሱ 54 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ዋንጫው የዩናይትድ ግስጋሴ ክፍያ
ማንቸስተር ዩናይትድ ካለፈው ኅዳር ጀምሮ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ሽንፈት የቀመሱት። ባለፉት ተከታታይ 9 ጨዋታዎች ደግሞ አልተሸነፉም።
ዩናይትድ ባለፈው ሐሙስ የስፔን ኃያሉን ባርሴሎና በመርታት በአውሮፓ ሊግ ወደ ዙር 16 ማለፍ ችሏል።
ፈረንሳዊው አጥቂ አንተኒ ማርሲያል በጉዳት በፍፃሜው የማይሳተፍ ሲሆን የቡድን የዘንድሮ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ማርከስ ራሽፈርድ ደግሞ የአካል ብቃቱ አጠራጣሪ ሆኗል።
አንግሊዝ የፊት መስመር ተጫዋች ከባርሴሎና ጋር በነበረው ፍልሚያ በ88ኛው ደቂቃ ተጎድቶ ሲወጥ እያነከሰ ታይቷል።
ምንም እንኳ ከዚህ ቀደምም በጉዳት ምክንያት ሙሉ ብቃቱን ባያሳይም ዘንድሮ ግን የማርከስ ራሽፈርድ ዓመት ይመስላል።
ራሽፈርድ፤ በሁሉም ውድድሮች ለቡድኑ 24 ጎል ሲያስቆጥር፤ ከዓለም ዋንጫ መልስ በትላልቅ የአውሮፓ ሊጎች በርካታ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋችም ሆኗል።
ባለፈው ዓመት ደካማ የሚባል አቋም የነበረው ማንችስተር ዩናይትድ ዘንድሮ የተሻለ ሆኖ ቀርቧል።
ዩናይትድ በሃገር ውስጥ ውድድር በኤፍ ኤ ዋንጫ እየተሳተፈ ሲገኝ የሊጉ መሪ አርሰናልና ሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ የሚጥሉ ፕሪሚዬር ሊጉን የማንሳት ተስፋም አለው።
ዩናይትዶች በ6 ዓመታት የመጀመሪያ ዋንጫቸውን የሚያነሱ ከሆነ እያሳዩት ላለው ግስግሴ ክፍያ የሚሆናቸው ይመስላል።
ሆላንዳዊው አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ቡድኑን ከተረከቡት ወዲህ ከፍተኛ መነቃቃት እንደፈጠሩ ብዙዎች እየመሰከሩላቸው ነው።
ኒውካስትል ‘አዲስ ታሪክ’ ሊሠራ ይችላል
ቢውካስትል በፕሪሚዬር ሊጉ ከቶተንሃም በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ አንድ ጨዋታ እየቀራቸው ከማንቸስተር ዩናይትድ በስምንት ነጥብ ርቀው ተቀምጠዋል።
ኒውካስትር በፕሪሚዬር ሊጉ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ካላቸው ቡድኖች መካከል ቁንጮ ናቸው።
በፈረንጆቹ ጥቅምት 2021 በሳዑዲ አራቢያ ባለሃብቶች እጅ ከወደቁ በኋላ አሠልጣኝ ኤዲ ሃው እንዲሁም በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ኒውካስትል ጠንካራ ቡድን እየገነቡ ነው።
ምንም እንኳ ብራዚላዊው ብሩኖ ጉዊማሬዥ ቅጣቱን ጨርሶ ለዋንጫው ቢመለስም ግብ ጠባቂው ኒክ ፖፕ ባለፈው ሳምንት ቀይ ካርድ በመመልከቱ በፍፃሜው አይሰለፍም።
ኒውካስትል ባለፈው እሑድ ከሊቨርፑል ጋር ባደረገው ፍልሚያ ሲረታ በ17 ጨዋታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የኒው ካስትል በረኛ ሆኖ እንደሚሰለፍ የሚጠበቀው የቀድሞው የሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ ሎሪስ ካሪዬስ ነው።
ኒውካስትል ለመጨረሻ ጊዜ ድል የተጎናፀፉት ባለፈው ጥር ሲሆን ባለፉት 11 ጨዋታዎች 9 ጎሎች ብቻ ማስቆጠራቸው ለኤዲ ሃው ስጋት ጭሯል።
‘ዌምብሊ የአሸናፊዎች ሥፍራ ነው’
የቀድሞው የኒውካስትልና የእንግሊዝ አጥቂ አለን ሺረር “እሑድ ዕለት ወደ ዌምብሊ ማቀናው ደጋፊ ሆኜ ቢሆንም ጫማዬን አጥልቄ ብጫወት እመኛለሁ” ይላል።
“ዌምብሊ የአሸናፊዎች ሥፍራ ነው። ዋንጫ ካላነሳህ ግን በጣም አስፈሪ ይሆንብሃል። ከተረታህ ለተጫዋቾችም ሆነ ለደጋፊዎች መጥፎ ስሜት የሚከናንብ ቦታ ነው።”
የቀድሞው የኒውካስትል ተከላካይ ስቲቨን ቴይለርም ይህን ይጋራል።
ለክሪስታል ፓላስ የተጫወተው የአየርላንድ ሪፐብሊኩ አጥቂ ክሊንተን ሞሪሰን ደግሞ ከባድ የፍፃሜ ጨዋታ እንደሚሆን ይገምታል።
“ኒውካስትል አስደናቂ አቋም ላይ ነው ያሉት። ብዙዎች ኤዲ ሃው የአጭር ጊዜ አሠልጣኝ ይሆናል የሚል ነበር ግምታቸው። ነገር ግን ቡድኑን ቀይሮታል። ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ማንንም መርታት እንደሚችሉ እያሰቡ ነው። ማርከስ ራሽፈርድ እንግሊዝ ውስጥ ጥሩ አቋም ያለው አጥቂ ነው። ጥሩ ጨዋታ እናያለን።”