የዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ በአገሪቱ ታሪክ የከፋው መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በአገሪቱ ታሪክ የከፋው መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
ከአውሮፓውያኑ ሐምሌ 30 ጀምሮ 3,605 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው ሲረጋገጥ 1,587 የሚሆኑት ሕይወታቸው አልፏል።
ወረርሽኙ 44% ለሕልፈት የሚዳርግበት ደረጃ ላይ ይገኛል። የአሁኑ ወረርሽኝ መነሻው ቡንዲቡግዮ የተባለው የቫይረሱ ዝርያ ነው።
ወረርሽኙ ከዚህ ቀደም ከ2018 እስከ 2020 ከተነሳው አንጻር የከፋው እንደሆነ ተገልጿል። በያዝነው ዓመት ወረርሽኙ መነሳቱ በይፋ የተገለጸው ግንቦት 15 ነበር።
ከ2018 እስከ 2020 በተነሳው ወረርሽኝ ወደ 3,500 የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 2,300 የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል።
አሁን ላይ ለቡንዲቡግዮ ዝርያ ፈቃድ የተሰጠው ክትባት የለም። ሆኖም በዩናይትድ ኪንግደም እና ሲንጋፖር ክትባቶች እየተሠሩ ነው።
ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ኢቦላ ባለፉት 50 ዓመታት በመላው አፍሪካ 15,000 ሰዎችን ገድሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ ወረርሽኙ "እየተስፋፋ እንደሚገኝ" እንዲሁም "የሚመዘገቡ ሞቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን" አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት ወረርሽኙ ከዚህ ቀደም ከነበረው ስርጭት ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበበት እንደሆነ ተገልጿል። ባለፈው ሳምንት ብቻ 567 ሰዎች በኢቦላ ሲያዙ 296 የሚሆኑ ሞተዋል።
ይሄ ቁጥር "ከፍተኛ ስርጭት መኖሩን" እንደሚያመለከት የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
የድርጅቱ መግለጫ "አለመረጋጋት፣ መፈናቀል እና ድንበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴዎች በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አሰናክለዋል፤ ስርጭቱንም አባብሰዋል" ይላል።
ወረርሽኙ የተነሳው በሰሜን ምሥራቅ ኢቱሪ ግዛት ሲሆን፤ አካባቢው ከደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ ጋር ይዋሰናል።
ወረርሽኙ ወደ ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል እና ወደ ደቡብ ኪቩ ግዛቶችም ተስፋፍቷል። እነዚህ አካባቢዎች በአመዛኙ በኤም23 ቁጥጥር ሥር ናቸው።
ኤም23 በሩዋንዳ የሚደገፍ ታጣቂ ቡድን ነው።
በኡጋንዳ 20 ሰዎች፤ በፈረንሳይ ደግሞ አንድ ሰው ኢቦላ ተገኝቶባቸዋል። ሁለት ሰዎች ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በቫይረሱ ተይዘው ጀርመን ታክመዋል።
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 30 የዓለም ጤና ድርጅት "እጅግ ተስፋ ሰጪ" ክትባት በሲንጋፖር እየተሠራ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ሌላ ክትባት ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም የሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛል።















