ማዕቀብ የተጣለበት የሩሲያ መርከብ ወደ ማሊ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን እያጓጓዘ መሆኑን ቢቢሲ አረጋገጠ

በሰሜናዊ ማሊ ከአማጺያን ጋር እየተዋጉ ያሉ የሩሲያ እና የማሊ ወታደሮች፣ ማዕቀብ በተጣለበት የጭነት መርከብ የተጓጓዙ የሚመስሉ በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እንደቀረቡላቸው ቢቢሲ ቬሪፋይ አረጋገጠ።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም. የማሊ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የለቀቀው እና ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ባረጋገጠው ቪዲዮ ላይ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ወደ ዋና ከተማዋ ባማኮ ሲገቡ ታይቷል። እነዚህ ተሽከርካሪዎች ቶጎ ውስጥ ከሚገኘው ሎሜ ወደብ እንደተነሱ ተገልጿል።
'ሚካኤል ብሪትኔቭ' የተሰኘው ማዕቀብ የተጣለበት መርከብ ሐምሌ 2 ቀን ሎሜ ወደብ መልሕቁን ጥሎ እንደነበር ቢቢሲ ቬሪፋይ የተመለከተው የመርከብ ጉዞ መከታተያ መረጃ አሳይቷል።
መርከቡ በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ሲሽከረከሩ የነበሩትን አይነት የጭነት መኪናዎች፣ መሣሪያ የተገጠመላቸው ሰው ማጓጓዣዎች እንዲሁም ቀላል የእግረኛ ወታደር ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን ይዞ እንደነበር የሳተላይት ምስሎች ማሳየታቸውን ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የመርከብ ጉዞ መከታተያ መረጃው እንደሚያስረዳው መርከቡ ሰኔ ላይ የተነሳው ከሩሲያ 'ባልቲይስክ' ወደብ ነው።
ወደ እንግሊዝ ካናል ሲደርስም በሩሲያ የጦር መርከብ ታጅቦ እንደነበር ቢቢሲ ቬሪፋይ ተገንዝቧል። የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች መምጣት በጂሃዲስት እና ተገንጣይ ቡድኖች ጥቃት ተከፍቶበት ለነበረው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት የምትሰጠውን ድጋፍ ማጠናከሯን ይጠቁማል።
ሩሲያ በጃማት ኑስራት አል ኢስላም ዋል ሙስሊሚን በተሰኘው ጂሃዲስት ቡድን እና ቱዋሬግ በተባለው ተገንጣይ ጥቃት ቡድን በከፈቷቸው ጥቃቶች በሰሜናዊ አገሪቱ ክፍል የሚገኝ ሠፊ ግዛትን ተቆጣጥረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የፈረንሳይ ጦር ከወጣ ወዲህ ለማሊ ወታደራዊ መንግሥት ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው ሩሲያ፣ በምላሹ የገንዘብ ክፍያ ተቀብላለች። በማዕድን እና በወርቅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ ቅድሚያ የማግኘት መብትንም አግኝታለች።
መጀመሪያ ላይ በማሊ ተሰማርቶ የነበረው 'ዋግነር' የተባለው የሩሲያ የቅጥረኛ ወታደር ኩባንያ ነበር። ኋላ ላይ ግን እንቅስቃሴዎቹ በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ስር በሚገኘው 'አፍሪካ ኮርፕስ' የተባለ አሃድ ተተክቷል።
ይህ ወታደራዊ አሃድ በማሊ አማጺያን ላይ የአየር ድብደባ ሲፈጽም የነበረ ቢሆንም፣ ታጣቂዎቹ ወደ ሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል የሚደርጉትን ጉዞ ማስቆም አልቻለም።
'አልደባራን ትሬት ኮንሰልታንትስ' የተባለው የአማካሪ ተቋም ትንታኝ የሆኑት ቻርሊ ዌርብ እንደሚናገሩት፤ አሁን ወደ አገሪቱ የደረሱት ተሽከርካሪዎች የማሊ እና የሩሲያ ኃይሎች በአማጺያኑ በአመፀኞች እጅ በወደቁት አካባቢዎች ጥቃት እንዲከፍቱ ያስችላቸዋል።
ጭነቱ የተጓጓዘበት 'ሚካኤል ብሪትኔቭ' የተባለው መርከብ 2024 ላይ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎበታል።
የጉዞ መከታተያ መረጃ እንደሚያሳየው መከርከቡ ከሁለት ሳምንት በፊት በእንግሊዝ ካናል ካለፈ በኋላ አቅጣጫ ጠቋሚውን አጥፍቶ ነበር። አቅጣጫ ጠቋሚው በድጋሚ የበራው ቶጎ ወደብ ላይ ለማረፍ ሲዘጋጅ ነው።
መርከቡ አጠቃላይ አገልግሎት የሚሰጡ የጭነት መኪናዎችን እንዲሁም በረት ለበስ እና ቀላል የእግረኛ ወታደር ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ጭኖ እንደነበር ከባልቲይስክ ወደብ ጉዞ ከመጀመሩ አስቀድሞ የተነሱ የሳተላይት ምስሎች ላይ ትንተና የሰሩ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የማሊ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጸው፣ ተሽከርካሪዎቹ እንደ ማሊ ሁሉ በሩሲያ የሚደገፍ ወታደራዊ መንግሥት ባላቸው ቶጎ እና ቡርኪና ፋሶ በኩል ተጓጉዘዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ለሎጅስቲክስ እና ለእቅድ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ለውጊያ ዘመቻዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ 'ጄንስ' የተባለው የመከላከያ መረጃ ተቋም ተንታኞች ገልጸዋል።
ባልቲይስክ ወደብ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለሚያጓጉዙ በርካታ መርከቦች መነሻ እንደሆነ ቢቢሲ ቬሪፋይ ተገንዝቧል።















