ሊዮኔል ሜሲ እና ሂላሪ ክሊንተን ከጆ ባይደን የአሜሪካ የነፃነት የክብር ሜዳሊያ ተሰጣቸው

ሂላሪ ክሊንተን ከጆ ባይደን ሜዳሊያ ሲቀበሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለአርጀንቲናዊው ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ እና ሂላሪ ክሊንተን የነፃነት የክብር ሽልማት ሰጥተዋል።

ድምፃዊው ቦኖ እና ቢሊየነሩ ጆርጅ ሶሮስ ከፕሬዝደንቱ የነፃነት የክብር ሜዳሊያ ከተሸለሙ ሰዎች መካከል ሆነዋል።

የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፣ ተዋንያኑ ዴንዜል ዋሺንግተንና ማይክል ጄ ፎክስ ዋይት ሐውስ በነበረው ሥነ-ሥርዓት ሜዳሊያ ተቀብለዋል።

በጠቅላላው 19 በባሕል፣ በፖለቲካ እና በተሟጋችነት ሥራ ያገለገሉ ሰዎች ሜዳሊያ ተሰጥቷቸዋል።

ዋይት ሐውስ እንዳለው ሜዳሊያ የተሰጣቸው ሰዎች " መልካም እና ለሀገራቸው እንዲሁም ለዓለም በጎ ሥራ የሰሩ" ናቸው።

አክሎ ሽልማት የተሰጣቸው ሰዎች "ለብልፅግና፣ ለእሴት እንዲሁም ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለዓለም ሰላም አስተዋፅዖ ያበረከቱ ናቸው" ብሏል።

የኢንተር ማያሚው እግር ኳስ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ የነፃነት የክብር ሜዳሊያ ከተሰጣቸውም መካከል ቢሆንም በሥፍራው አልነበረም።

ነገር ግን በተወካዩ በኩል በላከው መልዕክት "በሽልማቱ ከፍተኛ ክብር እንደተሰማው" ተናግሮ በሥፍራው ባለመገኘቱ ይቅርታ ጠይቋል።

ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእግር ኳስ እጅግ ምርጡ ተጫዋቹ የሚል ስያሜ የሚሰጠው የ37 ዓመቱ ሜሲ ስምንት ጊዜ የባለን ደኦር ሽልማት አግኝቷል፤ ስምንት ጊዜ ደግሞ የፊፋ ምርጡ ተጫዋች ተብሏል።

ዋይት ሐውስ ሜሲን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "ሜሲ በጤናው እና በትምህርቱ መስክ በመላው ዓለም በሊዮ ሜሲ ፋውንዴሽን አማካይነት ያገለግላል። የዩኒሴፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደርም ነው" ብሏል።

ባይደን ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት በአሜሪካ ለሲቪሎች የሚሰጠውን ከፍተኛ ክብር ባበረከቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ለተሸላሚዎቹ ያላቸውን ክብርና ምስጋና ገልፀዋል።

ከሂላሪ ክሊንተን እና ሊዮኔል ሜሲ በተጨማሪ የቀድሞው የሎስ አንጀለስ ሌከርስ የቅርጫት ኳስ ክለብ ተጫዋች ማጂክ ጆንሰን ሽልማቱን ተቀብሏል።

በፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወቅት የተቋቋመው ይህ የሜዳሊያ ሽልማት በፕሬዝደንቱ ጠቋሚነት እና በገለልተኛ አማካሪ አማካይነት የሚሰጥ ነው።

ከዚህ ቀደም አሜሪካዊቷ ጂምናስት ሲሞን ባይልስ፣ የኦስካር ተሸላሚዋ ተዋናይት ሚሼል የዎህ እና የአፕል መሥራቹ ስቲቭ ጆብስ ይህን ሽልማት አግኝተዋል።