ትራምፕ በፖርትላንድ ወታደሮች እንዲሰማሩና "ሙሉ ኃይላቸውን" እንዲጠቀሙ አዘዙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ትራምፕ የኢምግሬሽን ማቆያ ማዕከላትን ዒላማ ያደረጉ ተቃውሞዎችን ለማስቆም በኦሪገን ፖርትላንድ ወታደሮች እንዲሰማሩ እና አስፈላጊ ከሆነም "ሙሉ ኃይል እንዲጠቀሙ" አዘዙ።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ እርምጃው በአንቲፋ እና በሌሎች የአገር ውስጥ ሽብርተኞች በከበባ ውስጥ ያለውን የኢምግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከጥቃት ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።

ውሳኔው የትራምፕ አስተዳዳር ሕገ ወጥ ስደት ላይ እየወሰደ ባለው ጥብቅ እርምጃዎች ምክንያት በአሜሪካ ከተሞች የወታደሮች ስምሪት እየተስፋፋ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።

አሁን ላይ በፕሬዚደንቱ የተወሰደው እርምጃ ከዴሞክራቲክ ሕግ አውጭዎች ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን የፌደራል ወታደሮች በፖርትላንድ መሰማራታቸው አስፈላጊ አይደለም ብለዋል።

የኦሪገን ገዥ ቲና ኮቴክ "በፖርትላንድ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የለም።ማኅበረሰባችን ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተረጋጋ ነው" ብለዋል።

ኮቴክ ቅዳሜ እለት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ " ማንኛውም የወታደሮች ስምሪት ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ነው" ያሉ ሲሆን ለእርምጃው አስፈላጊ ምላሽ መስጠት ያስፈልግ እንደሆነ ለማየት ከኦሪገን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዳን ሬይፊልድ ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ምላሽ መስጠት ካለብን ለዚያ እንዘጋጃለን" ሲሉም አክለዋል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ፣ የብሔራዊ ዘብ አባላትን አሊያም የአሜሪካ ጦር አባላትን ይሁን የትኛውን የጸጥታ ኃይል የማሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ያልጠቀሱ ሲሆን "ሙሉ ኃይል መጠቀም" ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ አላብራሩም።

" በፕሬዚዳንቱ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት የአገር ውስጥ የደኅንነት መሥሪያ ቤት በፖርትላንድ የሚያካሂደውን ዘመቻ ለመደገፍ የአሜሪካ ጦር ሰራተኞችን ለማነቃነቅ ዝግጁ ነን" ሲሉ የፔንታገን ቃል አቀባይ ሲን ፓርንል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊና ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚሰጥም አክሏል።

በፖርትላንድ የሚገኘው የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተቋማት ከሰኔ ወር ጀምሮ በተቃዋሚዎች ኢላማ የሆኑ ሲሆን አንዳንዴም ወደ ተቃውሞው ወደ ግጭት አምርቶ ጉዳት አስከትሏል።

ከአውሮፓውያኑ መስከረም 8 ጀምሮም የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ በፖሊስ መኮንኖች ላይ ጥቃት መፈፀም፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ላለመዋል በመታገል እና እሳት በመለኮስ በ26 ግለሰቦች ላይ የፌደራል ክስ መስርቷል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት አርብ ዕለት እንደገለጸው ተቃዋሚዎች በፖርትላንድ በሚገኘው እና የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ተቋም ላይ በተደጋጋሚ ጥቃትና ከበባ ፈፅመዋል።

በዚህም በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና የፌደራል ሕግን በመጣስ ክስ እንደተመሰረተባቸው መሥሪያ ቤቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራው ጽሑፍ ገልጿል።

"በቅርቡ የአገር ውስጥ የሽብር ድርጅት ሆኖ የተፈረጀው ሮስ ሲቲ አንቲፋ በሕገ ወጥ መንገድ የስደተኛ ማዕከል መኮንኖች ላይ ድብደባ ፈፅሟል" ብሏል።

" የመኖሪያ ቤታቸውን አድራሻ በበይነ መረብ እና በበራሪ ወረቀቶች ላይ አትመዋል። ከአንቲፋ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችም በአገር ውስጥ ደኅንነት ሰራተኞች ላይ የግድያ ማስፈራሪያ ልከዋል" ሲል የአገር ውስጥ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም አንቲፋ የተባለው ቡድን የአገር ውስጥ የሽብር ድርጅት ሆኖ እንዲፈረጅ ትራምፕ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

'አንታይ ፋሺስት' [ፀረ ፋሽስት] - አንቲፋ በዋናነት በግራ እክራሪ አቀንቃኞች የተደራጀ እንቅስቃሴ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን በአሜሪካ ማንኛውም ቡድን በአገር ውስጥ የሽብር ድርጅት ሆኖ እንዲቋቋም የሚያስችል ምንም ዓይነት ሕጋዊ መንገድ የለም።

በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ፍረጃዎች የመናገር ነጻነትን እና የመሰብሰብ መብትን በሚጠብቀው ሕግ መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ተግዳሮቶች እንደሚገጥማቸው ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

ዴሞክራት ሕግ አውጭዎች የፕሬዚደንቱን ትዕዛዝ እና በኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ወኪሎች ላይ ተፈፅሟል የተባለውን ድርጊት ኮንነዋል።

የኦሪገን ሴናተር ሮን ዋይድን አርብ ዕለት ሲናገሩ የፌደራል ኃይሎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ በሞተው - ጆርጅ ፍሎይድ ግድያን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የፌደራል ፖሊሶች መሰማራታቸውን በማስታወስ የፌደራል ወኪሎች ከአምስት ዓመት በፊት የፈፀሙትን ጨዋታ እንደገና ሊመልሱት እንደሚችሉ የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎች አሉን ብለዋል።

በመሆኑም " የኦሪገን ነዋሪዎች ትራምፕ ግጭት ለመቀስቀስ በዘረጉት ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ እናስጠነቅቃለን" ብለዋል ሴናተሩ።

የአካባቢው ሕግ አውጭዎች ለማኅበረሰቡ አስጊ ያልሆኑ ሰዎችን በማሳደድ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ከስሰዋል።

"ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ኢላማ የሚያደርገው ወንጀል የሰሩ ሰዎችን ለማሰር እና በቁጥጥር ሥር ለማዋል ነው ብሏል።ይህንን ነው የነገሩን ፤ ነገር ግን እየተመለከትን ያለነው ይህንን አይደለም" ብለዋል የዲሞክራት ተወካይ የሆኑት ሱዛን ቦናሚሲ።

ለዚህም በልጁ ትምህርት ቤት ፊትለፊት የታሰረውን አባትን እና በኦሊምፒክ ብሔራዊ ደን የተነሳውን እሳት እየተጋፈጠ ባለበት የታሰረውን የእሳት አደጋ ሰራተኛን ጨምሮ በቅርቡ የተፈፀመ ክስተትን በዋቢነት አንስተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ፣ ዋሽንግተን በሚገኘው ካቶ ተቋም የታተመውን መረጃ ጠቅሰዋል።መረጃው በኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ከታሰሩት መካከል 65 በመቶ የሚሆኑ ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ እንዳልቀረበባቸው የሚያስረዳ ነው።

እርምጃው ምንም እንኳን በዴሞክራቶች ተቃውሞ ቢገጥመውም በአንዳንድ የሪፐብሊካን ባለሥልጣናት ድጋፍ አግኝቷል።

የአሜሪካ የሰራተኛ ሚኒስትር ሎሪ ቻቬዝ ዲሪመር ሕገ ወጥነት ፖርትላንድን ወደ የወንጀል መናሃሪያነት እንደቀየራት መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የኦሪገን የሪፐብሊካን ተወካይ ሆነው ያገለገሉት ቻቬዝ ትራምፕ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ተቋማትን ለመጠበቅ እና አሜሪካን ታላቅ ለማድረግ እርምጃ እየወሰዱ በመሆናቸው አመስግነዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ በሎስ አንጀለስ እና ዋሽንግተን ዲሲ የብሔራዊ ዘብ አባላትን አሰማርተዋል።በሚቀጥለው ሳምንትም የፌደራል ወኪሎች በቴኒስ ሜምፒስ እንደሚሰማሩ ይጠበቃል።

በሎስ አንጀለስ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለመያዝ በሚደረገው ሒደት የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ለመቆጣጠር 2ሺህ የፌደራል ወታደሮች እንዲሰማሩ ፕሬዚደንቱ አዘዋል። ለበርካታ ቀናትም ግጭቶች ተቀስቅሰው የነበረ ሲሆን ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ጥቅም ላይ ውሏል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በካሊፎርኒያ የሚገኙ የፌደራል ዳኛ በሎስ አንጀለስ የተደረገው የብሔራ ዘብ አባላት ስምሪት ሕገ ወጥ ነው ያሉ ሲሆን ለአገር ውስጥ ጉዳይ የጦር ኃይልን መጠቀምን በተመለከተ የፌደራል መንግሥት ያለውን ሥልጣን የሚወስነውን ሕግ የሚጥስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሆኖም ፕሬዚደንቱ በኦሪገን የፌደራል ኃይሎችን ለማሰማራት ሕጋዊ መሠረት ይኑራቸው አይኑራቸው ግልጽ አይደለም።