ሁለት የአሜሪካ ፖለቲከኞችን ለመግደል ሙከራ ያደረገው ተጠርጣሪ በፖሊስ እየታደነ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ ሚኒሶታ ሁለት የግዛቲቱ ሕግ አውጭዎች ዒላማ ከተደረጉ እና አንደኛዋ ፖለቲከኛ ከተገደለች በኋላ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ዘመቻ ተጀመረ።

የግዛቲቱ ገዢ ቲም ዋልትዝ "የታለመ የፖለቲካ ጥቃት" ባሉት በዚህ የግድያ ሙከራ ከሚኒሶታ ወጣ ባለ ስፍራ የ55 ዓመቷ የዲሞክራት ፖለቲከኛ መሊሳ ሆርትማን እና ባለቤታቸው ተገድለዋል።

ሌላኛው ፖለቲከኛ የ60 ዓመቱ ጆን ሆፍማን እና ባለቤታቸው በመኖሪያ ቤታቸው በጥይት በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ቀዶ ሕክምና ካደረጉ በኋላ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

የፖሊስ መኮንን በመምሰል ጥቃቱን የፈፀመው ተጠርጣሪ እየተፈለገ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

ተርጣሪው ቫንስ ሉተር ቦይልተር የተባለ የ57 ዓመት ግለሰብ መሆኑን ያሳወቀው ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር የሚያውል መረጃ ለሚያደርስ የ50 ሺህ ዶላር ሽልማት አቅርቧል።

በግዛቲቱ የሰው ሀብት ልማት ቦርድ ከሴናተር ሆፍማን ጋር የሰራው ተጠርጣሪው ሁለቱንም ፖለቲከኞች ያውቅ እንደሆነ እየተመረመረ ነው።

ፖሊስ ተጠርጣሪው ወደ ተጎጂዎች ቤት ሀሰተኛ የፖሊስ መታወቂያ በመያዝ እና የደንብ ልብስ በመልበስ እንዲሁም የአደጋ ጊዜ መብራቶች የተገጠመለት የፖሊስ የሚመስል ተሽከርካሪ በመያዝ አጭበርብሮ መግባቱን ገልጿል።

የድንገተኛ ጊዜ ጥሪ የደረሰው ፖሊስ ከተጠርጣሪው ጋር የተኩስ ልውውጥ ቢያደርግም አምልጧል።

የብሩክለን ፓርክ ፖሊስ አዛዥ ማርክ ቡርሌይ ፖሊስ ከአሜሪካ ምርመራ ተቋም (ኤፍቢአይ) እና ከድንገተኛ ምላሽ ሰጭዎች እንዲሁም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ፖሊሶች ጋር ተጠርጣሪውን የማደን ሰፊ ዘመቻ መጀመሩን ተናግረዋል።

አዛዡ ፖሊስ የተጠርጣሪውን ተሽከርካሪ መያዙን ጠቁመው ግለሰቡ በእግሩ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለው እንደሚያምኑም አክለው ተናግረዋል።

ባልስጣናቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ሁለት የፖሊስ መኮንኖች በጋራ ካልመጡ በስተቀር በራቸውን ለፖሊስ እንዳይከፍቱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በሁሉም የግዛቲቱ አካባቢዎች ተመራጭ ሹማምንት በተጠንቀቅ እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን፤ በተጠርጣሪው ተሽከርካሪ ዶናልድ ትራምፕን ለመቃወም የተጠራው ሰልፍ በራሪ ወረቀት መገኘቱን ተከትሎ ሰልፉ ተሰርዟል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት መግለጫ "እንዲህ ያለ ዘግናኝ ጥቃት በዩናይትድ ስቴት ተቀባይነት የለውም" ያሉ ሲሆን፤ "ባለስልጣናቱ በዚህ ድርጊት የተሳተፈውን ማንኛውንም ሰው ለሕግ ያቀርባሉ" ብለዋል።

የግዛቱ የሕዝብ ደኅንነት ኮሚሽነር ቦብ ጃኮብሰን የመንግሥት ሠራተኞች "በአመፅ እና በፈሪ መንገድ ዒላማ" መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ቅዳሜ ለሚኒሶታ "ጥቁር ቀን" ነበር፤ ነገር ግን "ፍርሃት ወይም ሁከት መለያችን ወይም እንዴት እንደምንሻገር መገለጫችን እንዲሆኑ አንፈቅድም" ብለዋል።

የሚኒሶታ ግዛት አስተደዳሪ ለጥቃቶቹ ምላሽ ለመስጠት ለድንገተኛ አደጋዎች አስተዳደር ጥቅም ላይ የሚለውን የአደጋ ጊዜ ማዕከል ከፍተዋል።

ገዥው ሚኒሶታ "ታላቅ መሪዎችን እኔ ደግሞ የቅርብ ጓደኞቼን አጥቻለሁ" ብለዋል።

በጥቃቱ ለተገደሉት ፖለቲከኛ የተለያዩ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ሐዘናቸውን እየገለፁ ናቸው።

መሊሳ ሆርትመን በሙያቸው ጠበቃ ሲሆኑ፤ በሚኒሶታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እ.አ.አ 2004 የተመረጡ እና ከ2019 ሕይወታቸው እስካለፈበት 2025 ድረስ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ነበሩ።