የትዊተር ተጠቃሚዎች ማየት የሚችሉት ‘ትዊት’ መገደቡን አለቃው ኢላን መስክ ገለጠ

ኢላን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ትዊተር ተጠቃሚዎች በቀን ማየት የሚችሉት የተወሰነ ‘ትዊት’ ብቻ መሆኑን ባለቤቱ ኢላን መስከ ገለጠ።

ኢላን በትዊተር ገፁ እንደገለጠው ሰማያዊ እርማት የሌላቸው [አንቬሪፋይድ] የትዊተር ተጠቃሚዎች በቀን ማየት የሚችሉት 1000 ትዊት ብቻ ነው።

ለትዊተር አዲስ የሆኑ ‘አንቬሪፋይድ’ ተጠቃሚዎች ደግሞ በቀን ከ500 በላይ እንዲያዩ አይፈቀድላቸውም።

ነገር ግን ሰማያዊ እርማት ያላቸው [ቬሪፋይድ] ተጠቃሚዎች በቀን እስከ 10 ሺህ ድረስ ማየት ይችላሉ።

ቢሊየነሩ ኢላን መጀመሪያ አስቀምጦት የነበረውን ገደብ በጥቂት ሰዓታትን አንስቶ አዲስ ሕግ አውጥቷል።

መስክ እንደሚለው ይህ ጊዜያዊ ገደቡ ትዊተር ያጋጠመውን ቴክኖሎጂያዊ ችግር ለመቅረፍ ያለመ ነው።

“ሰዎች ሥርዓቱን እየበዘበዙት ነው” ያለው መስክ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ኢላን መስክ መጀመሪያ ይህን ገደብ ሲገልጥ፤ ሰማያዊ እርማት የሌላቸው ተጠቃሚዎች በቀን 600 ትዊት ብቻ ነው ማየት የሚችሉት ብሎ ነበር።

ይህ ማለት እርሰዎ የትዊተር ተጠቃሚ ሆነው ሰማያዊ እርማት ከሌለዎትና በቀን 600 ጊዜ ትዊት ካዩ መተግበሪያው ‘ይቅርታ ለዛሬ ይበቃዎታል’ ብሎ ያሰናብቶታል።

ይህ የቢሊየነሩ የትዊተር ባለቤት እርምጃ ቅዳሜ ምሽት አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

በርካቶች ኢላን መስክ ይህን ያደረገበት አንድ ያልተፈታ ቴክኖሎጂያዊ ምክንያት አለው ብለው ያምናሉ።

የተቀሩት ደግሞ አወዛጋቢው ባለሃብት ሰዎች ትዊተርን ከፍለው አንዲጠቀሙ ማድረግ ስለሚሻ ነው የሚል ትንታኔ ያስቀምጣሉ።

‘ትዊተር ብሉ’ የተሰኘው ሥርዓት ተጠቃሚዎች ገንዘባቸውን ከፍለው ሰማያዊ እርማት እንዲያገኙ አሊያም ‘ቬሪፋይድ’ እንዲሆኑ ያስችላል።

መስክ ትዊተርን የግል ንብረቱ ከማድረጉ በፊት መተግበሪያው ለሰዎች ሰማያዊ እርማት የሚሰጠው የሚቀርብለትን ማመልከቻ በራሱ መርምሮ ነበር።

ነገር ግን አሁን በወር 8 ዶላር መክፈል የሚችል ተጠቃሚ ሰማያዊ እርማት ማግኘት ይችላል።

ቅዳሜ ዕለት ኢላን መስክ አዲሱን ገደብ ባስተዋወቀበት ወቅት በርካታ ተጠቃሚዎች ችግር አጋጥሞናል የሚል ‘ሪፖርት’ አቅርበዋል።

ኢላን መስክ በ44 ቢሊዮን ዶላር ትዊተርን ከገዛው በኋላ 8 ሺህ የነበረውን የድርጅቱ ሠራተኞች ቁጥር ወደ 1500 ዝቅ አድርጓል።