ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ እስራኤል በያዛቸው የፍልስጤማውያን ቦታዎች ዙሪያ የፍርድ ቤት አስተያየት እንዲሰጠው ጠየቀ
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እስራኤል በኃይል የያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕግ አስተያየት እንዲሰጠው ጠየቀ።
የሕግ አስተያየቱ እንዲጠየቅ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በ87 አገራት የተደገፈ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን ጨምሮ 26 አገሮች ደግሞ ተቃውመውታል።
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) ውሳኔዎችን ቢያስተላልፍም ሊያስፈጽማቸው ግን አይችልም።
የአርቡ ድምጽ አሰጣጥ ቤንጃሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ ከአንድ ቀን በኋላ የተካሄደ ነው።
እስራኤል ከጋዛ ብትወጣም አሁንም ዌስት ባንክን ተቆጣጥራለች። የተባበሩት መንግስታት አካባቢውን በኃይል እንደተቆጣጠረች ነው የሚመለከተው።
እስራኤል መላዋ እየሩሳሌምን ዋና ከተማዋ እንደሆነች ትገልጻለች። ፍልስጤማውያን ደግሞ ምስራቅ እየሩሳሌምን የወደፊቷ የፍልስጤም መንግሥት ዋና ከተማ ነች ይላሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ከተማዋ የእስራኤል ዋና ከተማ እንደሆነች ዕውቅና ከሰጡ ጥቂት አገሮች አንዷ ነች።
ፍልስጤማውያን ዌስት ባንክ፣ በእስራኤል በኃይል የተወሰደችው ምስራቃዊ እየሩሳሌም እና የጋዛ ሰርጥ የወደፊቷ የአገራችን አካል ናቸው ይላሉ።
የፍልስጤም ባለስልጣናት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የውሳኔ ሃሳብ ድል ነው ሲሉ አወድሰዋል። እስራኤል "በሕዝባችን ላይ ለምትፈጽመው ወንጀል ተጠያቂ የምትሆንበት ጊዜ አሁን ነው" ሲሉ ነቢል አቡ ሩዲነህ ተናግረዋል።
አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው ውሳኔው “የተዋረደ” ሲሉ ገልጸውታል።
ኔታንያሁ ቅዳሜ ማምሻውን እንደተናገሩት “የአይሁድ ሕዝብ በገዛ መሬታቸው ላይ ወራሪዎች አይደሉም። ዘላለማዊ በሆነችው ዋና ከተማችን እየሩሳሌምም ወራሪዎች አይደሉም። የትኛውም የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ያንን ታሪካዊ እውነት ሊያጣ አይችልም” ብለዋል።
ቤንጃሚን ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከአክራሪ ብሔርተኞች ጋር በመተባበር ወደ ስልጣን ተመልሰዋል።
ረቡዕ የታተመው የአዲሱ መንግሥት የመጀመሪያ መርህ "የአይሁድ ህዝብ በሁሉም የእስራኤል ምድር ላይ ብቸኛ እና የማያጠያይቅ መብት አለው" ሲል አውጇል።
ይህም የተቆጣጠሩትን ዌስት ባንክን የሚጨምር ሲሆን በአካባቢውም ሰፈራዎችን “ለማስተዋወቅ እና ለማልማት” ቃል ገብቷል።
እአአ በ1967 እስራኤል ዌስት ባንክን እና ምስራቅ እየሩሳሌምን ከተቆጣጠረች በኋላ ወደ 600,000 የሚጠጉ አይሁዶች አዲስ በተገነቡ 140 የሰፈራ አካባቢ ይኖራሉ።
አብዛኛው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰፈራውን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገ-ወጥ ቢላቸውም እስራኤል አበክራ ታጣጥለዋለች።
አዲሱ መንግሥት ያለ እስራኤል ፍቃድ የተገነቡ በዌስት ባንክ የሚገኙ 100 የሚጠጉ ግንባታዎችን ሕጋዊ ለማድረግ እና ዌስት ባንክን ለመቀላቀል ቃል ገብቷል።
በተመድ የዩናይትድ ኪንግደም ልዑካን ቃል አቀባይ ጉዳዩ ወደ አይሲጄ መቅረቡ “ሁለቱን ወገኖች ወደ ውይይት ለመመለስ ያግዛል” ብለው እንደማይሰማቸው ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ “ያለ ሁለቱም ወገኖች ስምምነት የሁለትዮሽ ውዝግቡ ምንድን ነው” በሚለው ላይ ምክር እንዲሰጥ መጠየቁ “አግባብ አይደለም” ሲሉም አክለዋል።