በሁለት ክለቦች ፍጥጫ ተቀያሪ ወንበር ለማሞቅ የተገደደው አንቶኒ ግሪዝማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አትሌቲኮ ማድሪድ ቅዳሜ ምሽት ከሴልታ ቪጎ ጋር ጨዋታውን አከናውኗል።
የማድሪዱ ክለብ ጨዋታውን 4 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።
አጥቂው አንቶኒ ግሪዝማን በዚህ ጨዋታም 62ኛው ደቂቃ ላይ ነው ተቀይሮ የገባው።
ፈረንሳዊው አጥቂ ዘንድሮ ዕጣ ፈንታው ከ30 ደቂቃ በታች መጫወት ሆኗል።
ባለፉት የላሊጋ ጨዋታዎች 28፣ 28፣ 26 እና 27 ደቂቃዎችን ብቻ ነው ሜዳ ውስጥ የቆየው።
ግሪዝማን በሁለት የስፔን ኃያላን ክለቦች የውል ግብግብ መሐል ለመቆት ተገዷል።
አጥቂው ቀደም ሲል የአትሌቲኮ ማድሪድ ተጫዋች ነበር።
ባርሴሎና እአአ በ2019 ከአትሌቲኮ ተጫዋቹን ለመዘዋወር ከ 100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ አውጥቷል።
በካምፕ ኑ ግን በሚፈለገው ደረጃ መንቀሳቀስ አልቻለም።
በዚህ ምክንያት ወደ እናት ክለቡ በወስት ተሰጠ።
በውሉ መሠረት አትሌቲኮ ማድሪድ በመጀመሪያ በውሰት ያጫውተዋል። ቀጥሎ የተለያዩ ሁኔታዎች ከተሟሉ ዝውውሩ ቋሚ ይሆናል ተብሏል።
በውሉ መሠረት ግሪዝማን በሁለት ዓመቱ የውሰት ዘመን ከሚሰለፍባቸው ጨዋታዎች 80 በመቶ ያህሉ ላይ ከ45 ደቂቃ በላይ ከተጫወተ አትሌቲኮ ማድሪድ ለባርሴሎና 35 ሚሊየን ፓውንድ ይከፍላል።
ታዲያ አትሌቲኮ ይህን ክፍያ ላለመፈጸም ነው ተጫዋቹን ከ30 ደቂቃ በታች ለማጫወት የተገደደው።
ባርሴሎና ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ መዘጋጀቱን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
እንድ ባርሴሎና ከሆነ ግሪዝማን ባለፈው የውድድር ዓመት ከ37 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 30ዎቹ ላይ ከ45 ደቂቃ በላይ ተሰልፏል ይላል። በውሉ መሠረት አትሌቲኮ ማድሪድ 40 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎኝ ተጫዋቹን በቋሚነት ማስፈርም አለበት ነው የባርሴሎና መከራከሪያ።
አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ ጉዳዩ ሌላ ነው ይላል። ግሪዝማን ከ45 ደቂቃ በላይ የተጫወተው በመጀመሪያው ዓመት መሆኑን ይጠቅሳል። ውሉ ተፈጻሚ እንዲሆን አጥቂው በሁለት ዓመቱ የውል ዘመን ከ80 በመቶ በላይ በሚሆኑ ጨዋታዎች ላይ ከ45 ደቂቃ በላይ መሰለፍ አለበት በሚል ይከራከራል።
በዚህ ምክንያት ነው ፈረንሳዊው ተጫዋች ዘንድሮ ከተቀያሪ ወንበር ላይ እየተነሳ ለመጫወት የተገደደው።
አትሌቲኮ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከፖርቶ ጋር በነበረው ጨዋታም ግሪዝማን ተቀይሮ ወደ ሜዳ ገበቷል።
በጨዋታው ባለቀ ሰዓት ባስቆጠረው ጎልም የዲዬጎ ሲሞኔ ቡድን ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።
ከጨዋታው በኋላ ግሪዝማን “የሚሆነው ነው የሆነው” ሲል ለሪፖርተሮች ተናግሯል።
“እኔ የምወስነው ጉዳይ አይደለም። ብዙ መጫወት እፈልጋለሁ። ሜዳ ስገባ ግን ያለኝን ሙሉ ለቡድኑ እሰጣለሁ። እዚህ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ። ማድረግ የምፈልገው ያለኝን በሙሉ ለቡድኑ፣ ለቾሎ (አሰልጣኝ ዲዬጎ ሲሞኔ) እና ደጋፊዎቹ መስጠት ነው” ብሏል።
ተጫዋቹ ዘንድሮ ከ60 ደቂቃ በኋላ ለምን ተቀይሮ ይገባል ተብለው የተጠየቁት አሰልጣኝ ዲዬጎ ሲሞኔ “አሁን ለአስር ዓመት ያህል ያወቃችሁኝ ይመስለኛል። እኔ የክለቤ ሰው ነኝ። በዚሁ መልኩም እቀጥላለሁ” ብለዋል።
ይህ ምላሽ ክለቡ ገንዘብ ላለመክፈል ከላይ የመጣን ትዕዛዝ አሰልጣኙ እያስፈጸሙ ነው በሚል በብዙዎች ተወስዷል።
ባርሴሎና የገንዘብ እጥረት ያለበት ክለብ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ሁለቱ በተደጋጋሚ የተገናኙ መሆኑን እና አትሌቲኮ ክፍያው እንዲቀነስለት ባርሴሎናን ጠይቋል።
አርብ ዕለት ስለጉዳዩ የተጠየቁት የባርሴሎናው አሰልጣኝ ዣቪ “ይህ እኔን አይመለከትም። ሁለቱን ክለቦች የሚመለከት ነው። እኔ የተሳተፍኩበት ጉዳይ አይደለም። ሁለቱ ክለቦች መነጋገር አለባቸው። ተጫዋቹ የአትሌቲኮ ንብረት ስለመሆኑ እርግጠኞች ነን” ሲሉ መልሰዋል።
ሲሞኔ ተጫዋቹ ለቀጣይ ጥቂት ዓመታት በቡድናቸው ውስጥ ቦታ እንዳለው ያምናሉ። አትሌቲኮ በቅርቡ 32 ዓመት ለሚሞላው ተጫዋች 40 ሚሊዮን ዩሮ መክፈሉን ግን አላመነበትም።
ባርሴሎናም ካለበት የገንዘብ እጥረት ጋር ተደማምሮ ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፈለውን ግሪዝማንን በድጋሚ ወደ ክለቡ የመመለስ ፍላጎት የለውም።
ግሪዝማን በባርሴሎና በቆየባቸው ሁለት ዓመታት 35 ጎሎችን በስሙ አስመዝገቧል።












