ኪም ጆንግ ኡን ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ ስትገናበው የቆየችውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አገልግሎት ላይ ለማዋል ዝግጁ ናት ሲሉ ኪም ጆንግ-ኡን ተናገሩ።
የሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ፤ ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ “ሊያጋጥማት ለሚችል ወታደራዊ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነች” በማለት ኪም ጁንግ ኡን መናገራቸውን መንግሥታዊው ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
ይህ የፒዮንግያንግ መሪ አስተያየት የተሰማው፤ ሰሜን ኮሪያ ለሰባተኛ ጊዜ የኒውክሌር ሙከራ ልታደርግ ትችላለች በተባለበት ጊዜ ነው።
አሜሪካ ከአንድ ወር በፊት ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ሙከራ ልታደርግ ትችላለች ስትል አስጠንቅቃ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ የኒውክሌር ሙከራ ያደረገችው እአአ 2017 ላይ ነበር። በቅርብ ጊዜያት በሁለቱ ኮሪያዎች ባሕረ ገብ መሬት ውጥረት አይሎ ቆይቷል።
በሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ልዩ ተወካይ የሆኑት ሱንግ ኪም፤ በአውሮፓውያኑ 2022 ሰሜን ኮሪያ ከተጠበቀው በላይ በርካታ የሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጓን ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ እአአ 2019 ላይ 25 ሙከራዎችን አድርጋ የነበረ ሲሆን፤ ባለፉት 7 ወራት ግን 31 የሚሳኤል ሙከራዎችን አከናውናለች ተብሏል።
ደቡብ ኮሪያ እያደገ ለመጣው የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ምላሽ ለመስጠት፤ ባለፈው ሰኔ ወር 8 ሚሳኤሎችን አስወንጭፋ ነበር።
ከእአአ 1950-53 የዘለቀው የኮሪያ ጦርነት ምንም እንኳ በተኩስ አቁም ስምምነት ቢቋጭም፤ ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ ላይ ድል መቀዳጀቷን ትገልጻለች።
ይህም “የድል-ቀን” በሰሜን ኮሪያ በየዓመቱ በወታደራዊ ትዕይንቶ፣ በሙዚቃ እና በርችት ታጅቦ ታስቦ ይውላል።
በመታሰቢያው ክብረ በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት ኪም ጆንግ ኡን፤ ከአሜሪካ በኩል ተደቅኖ ያለውን የኒውክሌር ጥቃት ለመከላከል፤ ሰሜን ኮሪያ እራሷን ለመከላከል “ታሪካዊ አስቸኳይ” የሆነ ተግባር ማከናወን ነበረባት ብለዋል።
ኪም አሜሪካ የአገራቸውን ወታደራዊ ልምምድ እንደ ትንኮሳ መቁጠሯም ስህተት ነው ብለዋል።
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ኪም፤ ደቡብ ኮሪያ በፒዮንግያንግ ላይ ጥቃት ብትሰነዝር የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ-ዬኦል አስተዳደር እና ጦሩ “ይደመሰሳል” ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንትን የተመለከተው ይህ የኪም አስተያየት፤ ምን ያህል በአዲሱ የደቡብ ኮሪያ መሪ ደስተኛ አለመሆናቸውን ያሳያል ተብሏል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ግንቦት 2014 ዓ.ም. ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በሰሜን ኮሪያ አማካይነት አገራቸው ላይ ሊቃጣ ከሚችል ስጋት እራስን መከላከል ያስችላል የተባለለትን ጠንከር ያለ ፖሊሲ አርቅቀዋል።
ይህ እራስን የመከላከል ፖሊሲ ደቡብ ኮሪያ የኒውክሌር ጥቃት አደጋ ውስጥ እንደሆነች ከታመነ፤ የአገሪቱ ኃይል ቀድሞ በሰሜን ኮሪያ ላይ እርምጃ መውሰድ ያስችለዋል።
ተንታኞች ሁለቱ ኮሪያዎች የገቡብት ውጥረት በቀጠናው ያሉ አገራት የጦር መሳሪያ ማበልጸግ እሽቅድድም ውስጥ የሚከት ነው ይላሉ።












