በአሜሪካ የከብት እርባታ ስፍራ በደረሰ ፍንዳታ 18 ሺህ ላሞች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, CASTRO COUNTY SHERIFF'S OFFICE
በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት በአንድ የከብት እርባታ ስፍራ ባጋጠመ ፍንዳታ 18 ሺህ ላሞች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ዲሚት ተብሎ ከሚጠራ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ሳውዝ ፎርክ የከብት እርባታ ስፍራ ያጋጠመው ፍንዳታ አንድ ሰው ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል።
ባለሥልጣናት በእርባታ ስፍራው ያለ ማሽን ሚቴን ጋስ እንዲፈነዳ በማድረጉ ጉዳቱ አጋጥሟል የሚል እምነት አላቸው።
በአሜሪካ በ2018 እና 2021 መካከል ባጋጠሙ የእሳት አደጋዎች ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ እንስሳት ሞተዋል።
የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ በከብት እርባታ ስፍራው እሳት መነሳቱ ሪፖርት ከደረሳቸው በኋላ በስፍራው ሲደርሱ አንድ ጉዳት የደረሰበትን ግለሰብ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ በፍንዳታው እና በጭስ ምክንያት በጠቅላላው የሞቱ ላሞች ቁጥር በትክክል ማወቅ ባይቻልም አሃዙ ከ18 ሺህ በላይ ሳይሞቱ አይቀርም ብሏል።
“የተረፉ ላሞች አሉ። ነገር ግን በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት መወገድ ያለባቸው ላሞች አሉ” ሲሉ የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ሳል ሪቬራ ለአካባቢ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የፖሊስ አዛዡ ሪቬራ እንዳሉት ከሆነ ለአደጋው መንስዔ የሆነው የከብት ቆሻሻ እና ውሃ የሚያስወግድ ማሽን በእሳት ከተያያ በኋላ የተከሰተ እንደሆነ መርማሪዎች ግምታቸውን ሰጥተዋል።
“ማሽኑ በኃይል ግሎ ከሚቴን ጋዝ ጋር ከተገናኛ በኋላ እሳቱ ተስፋፍቶ ፍንዳታ ሳያጋጥም አይቀርም” ብለዋል።
መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የእንስሳት ደኅንነት ተቋም የ18 ሺህ ላሞች ሞት ከተረጋገጠ፣ አደጋዎችን መመዝገብ ከመጀመረበት ከእአአ 2013 ጀምሮ በአንድ አደጋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከብቶች ያለቁበት ክስተት ይሆናል ብሏል።
ለእንስሳት መብት የሚቆረቆረው ተቋም የእርሻ ቦታዎች ላይ ለደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት እሳት አደጋ ለመከላከል ቅድሚያ መሰጠት አለበት ብሏል።
እንደ ደርጅቱ ከሆነ ከእአአ 2013 ጀምሮ 6.5 ሚሊዮን የእርባታ እንስሳት በእሳት አደጋ ምክንያት ያለቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 6 ሚሊዮኑ ዶሮዎች ሲሆኑ ወደ 7 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ላሞች ናቸው።












