ለ15 ዓመታት በግዞት የቆዩት የታይላንድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው ሲገቡ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለ15 ዓመታት በግዞት በውጭ አገር የቆዩት የታይላንድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታክሲን ሺናዋትራ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ታሰሩ።
ነገር ግን በርካቶች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለአጭር ጊዜ ብቻ በእስር ቤት እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው ስምምነት ከመንግሥት ጋር እንደፈጸሙ ያምናሉ።
ታክሲን ሺናዋትራ ወደ አገራቸው የገቡት በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ማለዳ በግል አውሮፕላናቸው ነው።
የ74 ዓመቱ ታክሲን ሁለት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡ ሲሆን በጎሮጎሳውያኑ 2006 በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣናቸው ተገርስሰዋል።
ከስልጣን ከተነሱ ከሁለት ዓመት በኋላም እሳቸው ፖለቲካዊ ናቸው በሚሏቸው የሙስና ወንጀል ሲከሰሱም ከአገር ሸሹ። ለዓመታትም በዱባይ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኑሯቸውን አድርገው ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅት በቀረቡባባቸው የወንጀል ክሶች እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣትም ተፈርዶባቸዋል።
በምርጫ አሸንፈው ወደ ስልጣን የመጡት ታክሲን በታይላንድ በጣም የተሳካላቸው እና የተፈሩ መሪ ነበሩ።
በአገሪቱ ያሉ ወግ አጥባቂ ንጉሳውያን ስርዓት ደጋፊዎችም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ማገዝን ጨምሮ አከራካሪ የፍርድ ቤት ሂደቶችን በመደገፍ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለማዳከምም ሲሰሩ ነበር ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በድፍረታቸው የሚታወቁት የቴሌኮሙ ባለጸጋ ተመልሰው መጥተዋል።
ፖለቲከኛው በባንኮክ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ሊቀበሏቸው መጥተው ነበር።
በሁለት ልጆቻቸው ታግዘውም ለአጭር ጊዜ በአየር ማረፊያ ላይ ቆይታ ያደረጉ ሲሆን ለንጉሳውያኑም ምስል አክብሮታቸውን ገልጸዋል።
ከአየር ማረፊያውም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወስደው በቀረቡባበው ክሶች ስምንት አመት ተፈርዶባቸዋል።
ወዲያውኑም ወደ ባንኮክክ ሪማንድ ማረሚያ ቤት እንደተወሰዱም ተገልጿል።
ማረሚያ ቤቱም ፖለቲከኛው ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑንም አስታውቋል።
ከዶን ሙአንግ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውጭ ፖለቲከኛውን ሲጠባበቁ ከነበሩት መካከል የ63 ዓመቱ ሳምኒያንግ ኮንግፖልፖርን አንደኛዋ ናቸው። እሳቸውንም ለማየት ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ሲጠባበቁም ነበር። እኚህ ግለሰብ እንደ ሌሎች በርካታ ደጋፊዎች ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የፖለቲከኛው ጠንካራ መሰረት ከሆነው ከሱሪን ግዛት ነው የመጡት።
“እስካሁን ካየናቸው ምርጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ምንም እንኳን ዛሬ እሳቸውን ላገኛቸውም ባልችልም ድጋፌን ለማሳየት ነው እዚህ የተገኘሁት” ብለዋል።












