የሩሲያ ሱፐርሶኒክ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በዩክሬን ድሮን ወደመ

በእሳት ተያያዘው ቦም ጣይ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, X (Twitter)

ታትሟል

የሩሲያ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በዩክሬን የድሮን ጥቃት መውደሙን ሪፖርቶች አመለከቱ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ እና ቢቢሲ የመረመራቸው ምስሎች የሩሲያው ኩባንያ ቱፖልቭ ስሪት የሆነው ቱ - 22 የጦር አውሮፕላን በደቡብ ሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው በሶልሲ 2 አየር ማረፊያ በእሳት ሲያያዝ አሳይተዋል።

ሞስኮ እንዳለችው ድሮኑ በቀላል መሣሪያ ተመትቶ የነበረ ቢሆንም አውሮፕላኑን ለማውደም ችሏል።

ዩክሬን ግን ክስተቱን በተመለከተ የሰጠችው አስተያየት የለም።

ቱ - 22 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ከድምጽ ፍጥነት በእጥፍ መጓዝ የሚችል ሲሆን ሩሲያ የዩክሬን ከተሞችን ለማጥቃት ስትጠቀምበት ቆይታለች ።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሰው አልባ አውሮፐላኑ ጥቃት የተፈፀመው ቅዳሜ ዕለት ሲሆን ቦታውም በኖቭጎሮድ ክልል ሶልሲ 2 ወታደራዊ አየር ማረፊያ ላይ ነው።

ሚኒስቴሩ ጨምሮም ሰው አልባ አውሮፕላኑ በአየር ኃይል ተቆጣጣሪዎች የታየ ሲሆን በትንሽ መሣሪያም ተመትቶ ነበር ብሏል።

“ በጥቃቱ አንድ አውሮፕላን የወደመ ሲሆን በዩክሬን የሽብር ድርጊት ምክንያት ሌላ የደረሰ ጉዳት የለም” ሲልም ገልጿል።

መግለጫው ጨምሮም በአየር ማረፊያ የፓርኪንግ ቦታ ላይ የተነሳውን እሳትም በፍጥነት መቆጣጠር ተችሏል ብሏል።

ሆኖም በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ቴሌግራም ላይ የተጋሩ ምስሎች ቱ - 22 አውሮፕላኑ በከፍተኛ እሳት ተያይዞ አሳይተዋል። ቢቢሲም ምስሉን የመረመረ ሲሆን ትክክለኛ ስለመሆኑም አረጋግጧል።

የአንድ አውሮፕላን ውድመት በሞስኮ አሁናዊ አቅም ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም እያደገ የመጣውን የኪዬቭን በሩሲያ ክልል ውስጥ ገብቶ ጥቃት የመፈፀም አቅም ያሳያል ተብሏል።

ኪዬቭ ከቅርብ ወራት ወዲህ ሞስኮን ለማጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ማይሎችን በመጓዝ በርካታ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶችን ከፍታለች።

ቅዳሜ ዕለት ጥቃት የተፈፀመበት ሶልሲ 2 ወታደራዊ አየር ማረፊያም ከዩክሬን ድንበር 650 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው።

ሆኖም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ሰው አልባ አውሮፕላኑ ርካሽ ፣ በገበያ ላይ የሚገኝና አጭር ርቀት የሚጓዝ ሲል ገልጾታል።

የዩክሬን ከተሞችን ለማጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋለውና በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተሰራው ሱፐርሶኒክ (ፈጣን) ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ቱ - 22 በኔቶ ‘ባክፋይር’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

የዚህ አውሮፕላን ዘመናዊ ስሪት ቱ 22ኤም3 የሚባል ሲሆን በሰዓት 2 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ ይችላል፤ የሚጣሉ ቦምቦችንና ሚሳይሎችን ጨምሮ 24 ሺህ ኪሎግራም የሚመዝን መሣሪያ መሸከም ይችላል።

ይህ የጦር አውሮፕላን በሶሪያ ፣ ቸቺንያ እና ጆርጂያ በቅርቡ ድግሞ በዩክሬን ጥቅም ላይ ውሏል።

የኪዬቭ አቃቤ ሕግ እንዳለው ጥር ወር ላይ ቱ - 22 የጣለችው ሚሳይል በዲኒፕሮ አንድ የመኖሪያ ሕንጻን መትቶ 30 ሰዎች ተገድለዋል።

ሰኞ ዕለት የዩክሬን መከላከያ ደኅንነት አገልግሎት ሌላ የጦር አውሮፕላን በሩሲያ ካሉጋ ክልል በድሮን ጥቃት መውደሙን የገለጸ ሲሆን፣ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃንም ጥቃቱን ዘግበው፣ ነገር ግን በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ገልጸዋል።