ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እሳት እንዲያጠፋ የተጠራው የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ በእሳቱ 10 ቤተሰቦቹን አጣ
አሜሪካ ውስጥ እሳት እንዲያጠፋ የተጠራው የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ በቦታው ሲደርስ እሳቱ የተነሳው ቤተሰቦቹ ቤት እንደሆነና 10 የቤተሰቡ አባላት አጣ።
ሦስት ሕጻናት እና ሰባት አዋቂዎች የነበሩበት ቤት በእሳት ጋይቶ ነው የአስሩ ሰዎች ሕይወት ያለፈው።
በአሜሪካ ፔንስልቬንያ የእሳት አደጋ ተከላካይ የሆነው ግለሰብ በቦታው ሲደርስ በእሳቱ የሞቱት ቤተሰቦቹ ሆነው አግኝቷቸዋል።
የእሳቱን መንስኤ ፖሊስ እያጣራ ይገኛል።
እሳቱ ከቤቱ በረንዳ አካባቢ እንደጀመረ ተገምቷል።
የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኛው ሀሮልድ ቤከር ይባላል።
በእሳት አደጋው ወንድና ሴት ልጁን፣ የባለቤቱን አባት፣ የባለቤቱን ወንድም፣ የባለቤቱን እህት፣ ሦስት የልጅ ልጆቹን እና ሁለት ሌሎች ዘመዶቹን ማጣቱን ተናግሯል።
የሞቱት ሁለት ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ነበር የሄዱት።
ፖሊስ እንዳለው ከሞቱት መካከል የ19፣ የ22፣ የ79 እና የ53 ዓመት ሰዎች ይገኙበታል።
የሀሮልድ ልጅ ዴል የአባቱን ፈልግ ተከትሎ እሳት አደጋ ተከላካይ ሆኖ ነበር።
የሞቱት ሰዎች አስክሬን የተገኛው በአነፍናፊ ውሾች ድጋፍ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።
በቤቱ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሦስት አዋቂዎች ከአደጋው ማምለጥ ችለዋል።
“የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥት ሞክረዋል። ግን ቤቱ ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ እሳቱ መልሷቸዋል” ሲሉ የፔንስልቬንያ ፖሊስ ሉተነንት ዴሬክ ፌልስማን ተናግረዋል።
ቤተሰቦቹን ያጣው የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ፣ አደጋው ከተከሰተበት ቦታ ከተደወለላቸው በኋላ ወደ ስፍራው ሲቃረቡ በእሳት የተያያዘው የቤተሰቦቹ ቤት እንደሆነ እንዳወቀ ሲቲዝንስ ቮይስ ለተባለ ጋዜጣ ተናግሯል።
“ልክ መኪናውን ስናቆም መላው አካባቢው እሳት ለብሷል። ልናተርፋቸው ሞክረን ነበር። እዚያ የነበሩት ሁለቱ ልጆቼና ሌሎቹም ልጆች ለቤተሰብ ጥየቃ ነበር የመጡት” ብሏል።
የፔንሰልቬንያ ከንቲባ ቶም ውልፍ “በእሳት አደጋው ልቤ ተሰብሯል” ሲሉ ትዊት አድርገዋል።
የአሜሪካ ቀይ መስቀል በእሳቱ የተነሳ ለተጎዱ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ለሲኤንኤን ገልጿል።