የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት፣ 'ፑቲን ሊያስገድሉኝ ነበር' በሚል የልዩ ጥበቃ አዛዣቸውን አባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Eugen Kotenko / Ukrinform/Future Publishing via Getty Image
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ የግል ጥበቃ የሚያደርግላቸውን ‘ሪፐብሊካን ጋርድ’ ኃላፊን አባረሩ።
ይህን እርምጃ የወሰዱት ሁለት ከፍተኛ የዩክሬን የጦር መኮንኖች እሳቸውን በማስገደል ሴራ ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ነው።
የግል ጥበቃ የሚያደርግላቸውን ቡድን የሚመራው ሰው ሜጀር ጄኔራል ሰርሂ ረድ ይባላሉ። ከ2019 ጀምሮ በዚሁ የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።
ዜለንስኪ ኃላፊውን ካባረሩ በኋላ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
ይሁንና ‘የሪፐብሊካን ጋርድ’ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደረሰበት በተባለው የግድያ ሴራ ምክንያት የዜለንስኪም ሆነ ሌሎች ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸው ሕይወት አደጋ ላይ እንዳለ ተረድቷል።
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ እንደሚሉት በቅርቡ ፑቲን እሳቸውንና ሌሎች ሁለት የደኅንነት ባለሥልጣኖቻቸውን ሊያስገድሉ የጎነጎኑት ሴራ በመጨረሻው ሰዓት ተደርሶበታል።
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪን ለመግደል ትእዛዝ ተቀብለው ነበር የተባሉት ሁለቱ የዩክሬን ከፍተኛ ኮሎኔሎች የሩሲያውን ዝነኛውን ኬጂቢ ተክቶ በሚሠራውና በምህጻሩ ‘ኤፍኤስቢ’ ተብሎ በሚጠራው የስለላና ደኅንነት አገልግሎት ነበር የተመለመሉት ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በተደጋጋሚ ሩሲያ ልታስገድላቸው ሙከራ እንደምታደርግ ተናግረዋል። ሆኖም በቅርቡ ተደረሰበት የተባለው ሴራ ከሁሉም አስደንጋጩ እንደሆነ ነው የተዘገበው።
ከፕሬዝዳንቱ ሌላ የዩክሬን ወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊ የሆኑትን ከይሪሎ ቡዳኖቭን እንዲሁም የአገሪቱ ጠቅላላ የደኅንነት ኃላፊ ቫሲል ማላዩክን ዒላማ ያደረገ ነበር።
የደኅንነት ኃላፊው በዚህ ሳምንት እንደተናገሩት የግድያ ሙከራው ባይደረስበት ኖሮ፥ ፑቲን ለ5ኛ ጊዜ ቃለ መሐላ ከመፈጸማቸው በፊት ሊቀርብ የነበረ ‘ውድ ስጦታ’ ነበር።
የዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደሚለው ሴራው የነበረው ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪን በገዛ ጠባቂዎቻቸው በኩል አፍኖ መውሰድና መግደል ሲሆን ወታደራዊ መኮንኑ ቡዳኖቭ ደግሞ በሮኬት እንዲመቱ ነበር የታሰበው።
የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ኃላፊ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል ሰርሂ ረድ የ47 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ ምናልባት የተባረሩት ሴራው ውስጥ ነበሩበት ተብለው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ሁለቱ የዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች አንዱ የሆኑት፣ የአንድሪ ሁክ የቅርብ ጓደኛ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል።
የዩክሬን ሚዲያዎች እንደዘገቡት ሁለቱ ሰዎች ወታደራዊ ትምህርት ቤት አብረው ነው የተማሩት።
የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሰርሂ ረድ በዩክሬን ወታደራዊ አግልግሎት ነው ዕድሜያቸውን በሙሉ ያሳለፉት። በዋናነት ደግሞ የደኅንነት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ነው የቆዩት።
ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ወረራ ስትከፍት ልዩ ኮማንዶዎቿ ኪየቭ በቀጥታ እንዲያርፉ ከሞከረች ጀምሮ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪን ለማስገደል ብዙ ሙከራዎች አድርጋለች ይላሉ የዩክሬን ባለሥልጣናት።
የሩሲያን የግድያ ሴራ በመፍራት ይመስላል ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በተደጋጋሚ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን በመቀያየር ይታወቃሉ።
በቅርቡ እንኳን የልዩ ኃይል አዛዥ ኮማንደር የሆኑትን ኮሎኔል ሰርሂ ሉፓንቹክን ለወራት እንኳ ሳያገለግሉ አንስተዋቸዋል።
የዩክሬን ወረራ ከተፈጸ ወዲህ ባሉ ሁለት ዓመታት የጦር አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ቫለሪ ዛሉሽኒ በተመሳሳይ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በየካቲት ወር ነበር።
ጄኔራል ቫለሪ አሁን በዩኬ የዩክሬን አምባሳደር ናቸው።












