በዩክሬን ጦርነት ለሩሲያ ወግነው የሚዋጉ ቢያንስ 100 ሰሜን ኮሪያውያን ወታደሮች መገደላቸው ተነገረ

የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዩክሬን ጦርነት ለሩሲያ ወግነው ከሚዋጉት መካከል ቢያንስ 100 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መገደላቸውን የደቡብ ኮሪያ የፓርላማ አባል ገለጹ።

ፓርላማው በአገሪቱ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ማብራሪያ ከተሰጠው በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ሊ ሱንግ ኳን ተጨማሪ 1 ሺህ ወታደሮች ቆስለዋል ብለዋል።

ከተገደሉት መካከል ከፍተኛ መኮንኖች እንደሚገኙበት ተናግረው የወታደሮቹ ግድያ ስለ አካባቢው በቂ ግንዛቤ አለመኖር እንዲሁም ከሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ጋር በተያያዘ ሊገለጽ ይችላል ብለዋል።

በጦርነቱ የተገደሉ ሰሜን ኮሪያውያን ወታደሮች ሪፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው። በጥቅምት ወር ሰሜን ኮሪያ 10 ሺህ ወታደሯቿን ሩሲያን ለማገዝ መላኳ ተገልጿል።

ሰኞ ዕለት የአሜሪካ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ትክክለኛ ቁጥር ሳይገልጹ ሰሜን ኮሪያውያን ወታደሮች ተገድለዋል ብለው ነበር። ከአንድ ቀን በኋላ ስማቸው ያልተጠቀሰ አሜሪካዊ ባለስልጣን "በርካታ መቶዎች" ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ብለዋል።

ቢቢሲ ተገድለዋል የተባሉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ሪፖርት በገለልተኛነት አላረጋገጠም።

አንዳቸውም ከዚህ በፊት የውጊያ ልምድ እንደሌላቸው የሚታሰብ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የመጀመሪያዎቹን ሳምንታት በሩሲያ በስልጠና ላይ እንዲሁም በድጋፍ ሰጪነት ተሰማርተው እንደነበር ይታመናል።

ዩክሬን በሩሲያ የከርስክ ግዛት ድንገተኛ ወረራ በመፈጸም የተቆጣጠረቻቸውን ስፍራዎች ላይ ወታደሮቹ ተገድለው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።

ባለፈው ቅዳሜ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ በከርስክ ግዛት እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰሜን ኮሪያውን ወታደሮችን ማሰማራት ጀምራለች ብለው ነበር።

በቅርብ ወራት የሩሲያ ወታደሮች በምስራቃዊቷ የዩክሬን ክፍሎች እየገሰገሱ ሲሆን የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች የዚህ ስምሪት አካል እንዳልሆኑ ይታሰባል።

ሊ ሱንግ ኳን ለተጨማሪ ስምሪቶች ዝግጅቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ሪፖርቶችን ጠቅሰው የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ስልጠናውን በበላይነት ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ሩሲያም ሆነ ሰሜን ኮሪያ ወታደሮቹ መሰማራታቸውን ዕውቅና አልሰጡም። ነገር ግን መንግሥታዊ የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ ሐሙስ ዕለት ያሰራጨው የሰሜን ኮሪያ መግለጫ አገሪቱ ከሩሲያ ጋር ያላት አጋርነት "የአሜሪካ እና የምዕራቡ ዓለም ያሰቡትን ተጽእኖ እያደናቀፈው ነው" ብሏል።