በሞስኮ መሃል ከተማ የሚገኝ ሕንጻ በዩክሬን ድሮን ከተመታ በኋላ በረራዎች ተሰረዙ

ታትሟል

በማዕከላዊ ሞስኮ በግንባታ ላይ የነበረ ሕንጻ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መመታቱን የከተማዋ ከንቲባ ሰርጊ ሶባያኒን አስታወቁ።

በሌላ በኩል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በሞስኮ ሞዛይስክ እና ካሃይሚኪ በተባሉ ግዛቶች ሁለት ድሮኖች በአየር ኃይሉ ተመትተው መጣላቸውን አስታውቋል።

በሞስኮ መሃል ከተማ በሚገኘው ሕንጻ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በሰው ላይ ሰለደረሰው ጉዳት የተባለ ነገር የለም።

የሩሲያ ባለሰልጣናት ክስተቱን “በኪዬቭ አስተዳደር የተፈጸመ የሽብር ጥቃት” ሲሉ ገልጸውታል።

ዩክሬን ብዙ ጊዜ በሩሲያ ግዛት ውስጥ ስለምትፈጽማቸው ጥቃቶች በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ትቆጠባለች።

የዚህ የድሮን ጥቃት ተከተሎ ወደ ሞስኮ የሚደረጉም ሆነ ከሞስኮ የሚነሱ በረራዎችን ታግደው ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሞስኮ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ሲፈጸሙባት አየር ማረፊያዎቿን መዝጋት በተደጋጋሚ የምትወስደው እርምጃ ሆኗል።

በሩሲያ መዲና ሞስኮ በምሽት መሰል የድሮን ጥቃት በተከታታይ ሲፈጸም ይህ ለ6ኛ ጊዜ መሆኑን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በግንባታ ላይ ያለ ሕንጻን ስለመታው ድሮን አስተያት ሲሰጥ ድሮኑ በኤለክትሮኒክ ዘዴ ጫና ውስጥ እንዲውድቅ መደረጉን እና በዚያ ምክንያት ከቁጥጥር ውጪ ሀኖ ከሕንጻው ጋር መላተሙን ገልጿል።

ባለ አምት ወለል የሆነው ሕንጻ በጥቃቱ ምክንያት በርካታ መስታወቶች መርገፋቸውን እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ክትትል እያደረጉ እንደሆነ ከንቲባው ጠቅሰዋል።

ዋሽንግተን ተመተው የተጣሉት ድሮኖች አስመለክቶ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በሰጠችው አስተያየት ሩሲያ ውስጥ የሚፈጸም የድሮን ጥቃትን እንደማታበረታታ ገልጻለች።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ዩክሬን ራሷን እንዴት መከላከል እንዳለባት እራሷ ነች መወሰን ያለባት ሲሉ የሚደመጡ ሲሆን ሩሲያ ወታደሮቿን ከዩክሬን በማስወጣት ጦርነቱን በየትኛውም ሰዓት መቋጨት ትችላለች ይላሉ።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በሩሲያ የድሮን ጥቃት ደርሷል የሚለው ክስ እየጨመረ መጥቷል።

ባለፈው ማክሰኞ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በሞስኮ ሁለት ድሮኖችን መትቶ መጣሉን እና ሌሎች ሁለት ድሮኖችን ደግሞ ዩክሬን ደምበር አቅራቢያ ማጨናገፉን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ጨምሮም የሩሲያ የጦር አውሮፕላን በጥቁር ባሕር የሩሲያ ጋዝ ማምረቻ ጋር የታየውን የዩክሬን የጦር ጀልባ ማውደሙን ገልጿል።

ትላንት ሞስኮ ላይ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ የዩክሬን ባለስልጣናት አስተያየት ባይሰጡም የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ቀደም ብሎ በሰነዘሩት አስተያየት በሩሲያ ግዛት የሚፈጸመው ጥቃት “የማይቀለበስ፣ ተፈጥሯዊና ፍጹም ፍትሃዊ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።