ኡበር ከ550 በላይ በሚሆኑ ሴቶች በወሲባዊ ጥቃት ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኡበር ከ550 በላይ የሚሆኑ ሴቶች በአሽከርካሪዎቹ “ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሞብናል” ሲሉ በአሜሪካ ክስ አቅርበዋል።
በሴት ተሳፋሪዎች የቀረበው ክስ “መደፈር፣ ማንጓጠጥ፣ መታገት፣ መደብደብ፣ በሃሰት ማሳሰር” እና ሌሎች ተጨማሪ ክሶችን አካትቷል።
ትናንት ሳንፍራሲስኮ ግዛት በሚገኘው ፍርድ ቤት የቀረበውን ይህ ክስ በተመለከተ የኡበር ቃል አቀባይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ወሲባዊ ጥቃት እጅግ ሰቅጣጭ ወንጀል ነው፤ በመሆኑም እያንዳንዱን ቅሬታ በአንክሮ እንመለከተዋለን” ብለዋል።
“ከደህንነት የበለጠ ምንም አስፈላጊ ነገር የለም። ለዚህም ኡበር አዳዲስ የደኅንነት መጠበቂያ ሥራዎችን ሰርቷል። ለአንዳንድ ከፍተኛ ክስተቶችም ግልጽነትን አስፍኗል። ምንም እንኳን በሂደት ላይ ባለው ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ብንቸገርም ደኅንነትን በተመለከተ ግን ከልባችን በርትተን እንሰራለን” ብለዋል።
ወሲባዊ ጥቃቱ የአንድ አካባቢ ክስተት ብቻ ሳይሆን በብዙዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች የሚፈጸም መሆኑ ተገልጿል።
ኡበር አሁን በሳንፍራንሲስኮ ከቀረበበት ክስ በተጨማሪ ሌሎች 150 የሚሆኑ ክሶች ቀርበው ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። የቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው የኡበር አሽከርካሪዎች ከአውሮፖውያኑ 2014 በፊት ጀምሮ ሴት ተሳፋሪዎችን በመድፈር እና ጾታዊ ጥቃት በማድረስ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
ወሲባዊ ጥቃትን በተመለከተ በኩባንያው ላይ የሚደርሰው ቅሬታ ከዓመታት በፊት የጀመረ ቢሆንም ኩባንያው የቀረበበትን ክስ መሰረት አድርጎ የደኅንነት ማሻሻያ ከማድረግ ይልቅ ‘መበልጸግን’ አስቀድሟል ተብሏል።
“ባለፈው ወር ኡበር የ2020ን ሁለተኛውን የአሜሪካ የደኅንነት ሪፖርት አቅርቦ ነበር። ሪፖርቱ እንዳሳየው 998 የወሲባዊ ጥቃት ክሶች የቀረቡ ሲሆን 141 የሚሆኑት መደፈር ናቸው።
ኩባንያው ከ2019 እስከ 2020 ባቀረበው ሪፖርት አምስት የከፋ ወሲባዊ ጥቃት በሚፈጸምባቸው ዘርፎች በአጠቃላይ 3 ሺህ 824 ወሲባዊ ጥቃት ሪፖርት መቀበሉን ይፋ አድርጓል።
ከ2017 እስከ 2018 በነበረው ሪፖርትም ኩባንያው 5 ሺህ 981 ከወሲባዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ ሪፖርቶች እንደደረሱት ገልጿል።
ኡበር ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሴት ተሳፋሪዎችን የሰውነት አካል ያለ ፈቃድ ከመሳም እስከ መድፈር እንደሚደርስም ቅሬታ አቅራቢዎች ገልጸዋል።












