የሲሪላንካው ጠቅላይ ሚኒስትር ጦር ኃይሉ ሥርዓት እንዲያስከብር አዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ጥሰው የገቡት የሲሪላንካ ተቃዋሚዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮም በተመሳሳይ መልኩ መውረራቸውን ተከትሎ ጦሩ ሥርዓት እንዲያስከብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ አስተላለፉ።
የሲሪላንካ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክሪሜሲንግ በአገሪቱን ሥርዓት ለመመለስ አስፈላጊውን ሁሉ ጦሩ እንዲያደርግም ነው ባስተላለፉት ትዕዛዝ ያስታወቁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል በጦር አውሮፕላን ከአገር በኮበለሉት ፕሬዚዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ አማካኝነት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል።
ነገር ግን እሳቸው በኃላፊነት መሾማቸው ተቃዋሚዎችን ደስ አላሰኘም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሥልጣን መነሳት አለባቸው የሚሉ ተጨማሪ ተቃውሞዎችን አስነስቷል።
ሲሪላንካ ባለፉት አሥርት ዓመታት በከፋ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ስትናጥ ቆይታለች።
የሲሪላንካ አብዛኛው ሕዝብ ለዚህ ቀውስ የጎታባያ ራጃፓክሳን አስተዳደር ተጠያቂ የሚያደርግ ሲሆን በያዝነው ዓመት ግንቦት ወር፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ራኒል ዊክሬሜሲንግንም የችግሩ አካል አድርገው ይመለከቷቸዋል።
ተቃዋሚዎች በአስተዳደሩ ላይ ያላቸውን ቅያሜም ለመግለጽ የራሳቸው እርምጃ የሚሉትን እየወሰዱ ሲሆን፣ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜም ረቡዕ ዕለት ደኅንነቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቅ የመንግሥት ህንፃን ጥሰው ገብተዋል። ይህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ነበር።
ከዚያ በፊት ተቃዋሚዎቹ ኢላማ አድርገው የነበረው የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ሲሆን በፕሬዚዳንት ራጃፓክሳ መኖሪያ ቤት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገሪቱን ሰንደቅ አላማ የያዘ ሕዝብ መፈክሮችን በማሰማት አጥሩን ጥሰው ገብተዋል።
ከስፍራው የወጣ ቪዲዮ ተቃዋሚዎች በግቢው ውስጥ ሲዘዋወሩ እና በፕሬዚዳንቱ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሲዋኙ፣ ሌሎች ደግሞ የፕሬዚዳንቱን እቃዎች ሲበረብሩ እንዲሁም አንዳንዶች የቅንጦት መታጠቢያ ቤታቸውን ሲጠቀሙ ያሳያል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሮ በተመሳሳይ መልኩ ወንበሮቻቸው ላይ ወጥተው ፎቶ ሲነሱ እንዲሁም ሰንደቅ አላማ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ተቃዋሚዎች ጥሰው የገቡትን ቢሯቸውን እና ሌሎች የመንግሥት ህንጻዎችን ለቀው እንዲወጡ እና ከባለሥልጣናት ጋር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
“ሕገ መንግሥታችንን ማፍረስ አንችልም። ፋሺስቶች ሥልጣን እንዲረከቡ መፍቀድ አንችልም። ይህንን የዲሞክራሲ ስጋት የሆነው ፋሺስታዊ ሂደት ማብቃት አለበት” ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትዕዛዝ ተከትሎ ጦሩ አገሪቷን ሊቆጣጠር እንደሚችል አመላካች እንደሆነ የተጠየቁት በኮሎምቦ የሚገኙት የሰብአዊ መብት ጠበቃ ብሃቫኒ ፎንሴካ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በሲሪላንካ ከሌሎች የጎረቤት አገራት በተለየ መልኩ “ጦሩ በፖለቲካም ሆነ በመንግሥት ሚና የተጫወተበት አገሪቱ ታሪክ የላትም” ብለዋል።
አክለውም “በጣም ጠንካራ ዲሞክራሲ ነበረን እና በዚህም ሂደት ተወካዮች ተመርጠው ነበር። በአሁኑ ወቅት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፤ ስለዚህ ሁሉም ነገር ይቻላል” ሲሉ አክለዋል።












