በአሜሪካ በመደፈር ያረገዘችው የ10 ዓመቷ ህጻን ጽንስ ማቋረጥ መከልከሏ አነጋጋሪ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, የፍራንክሊን ፍርድ ቤት ማቆያ
በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት በደረሰባት የመደፈር ጥቃት አማካኝነት የስድስት ሳምንት ነፍሰ ጡር የሆነች አንዲት ታዳጊ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ምክንያት ጽንሱን በግዛቱ ማቋረጥ ያለመቻሏ አለማቀፍ መነጋገሪያ ሆኗል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ 27 ግዛቶች ከዚህ በፊት ሕገ-መንግስታዊ መብት ሆኖ የቆየውን ጽንስ የማቋረጥ መብትን አግደዋል። ታዳጊዋ በህጻናት ጥቃት ሃኪም ሪፈር ከተጻፈላት በኋላ ወደ ኢንዲያና ፖሊስ ከተማ በመጓዝ አገልግሎቱን እንዳገኘችም ተዘግቧል። ነገር ግን እስካሁን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ክልከላውን ማስፈጸም ባልጀመሩ ግዛቶችም እገዳውን ለማስፈጸም ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ተጠርጣሪው ጌርሾን ፉንቴስ በያዝነው ሳምንት ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ፖሊስ ድርጊቱን መፈጸሙን አምኗል ሲል ኮሎምበስ ዲስፓች ዘግቧል።
የጓቲማላ ስደተኛ የሆነው ግለሰቡ ወደ አሜሪካ የገባው በሕገ-ወጥ መንገድ እንደሆነ የዘገበው ደግሞ ፎክስ ኒውስ ነው።
ፍርድ ቤትም ግለሰቡ ሊጠፋ ይችል ይሆናል ወይም ሌላ ሕጻን ላይ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል ከሚል ስጋት የዋስትና መጠኑን 2 ሚሊዮን ዶላር በማድረጉ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ሆኖ ሂደቱን እንዲከታተል አድርጓል። በወንጀሉ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቀዋል። ጉዳዩን ወደ ትኩረት ያመጡት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ባሳለፍነው አርብ በዋይት ሃውስ ባደረጉት ንግግር ወቅት ሲሆን ''ልጅቷን ሆናችሁ አስቡት'' ሲሉም በቁጣ ተናግረው ነበር።








