አሜሪካ ለደቡብ አፍሪካ የኤችአይቪ መርሃ ግብሮች የምትሰጠውን ድጋፍ ልታቋርጥ ነው

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ የኤችአይቪ እና ኤድስን ሥርጭት ለመግታት ለተዘረጉ መርሃ ግብሮች ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ እንደሚያቋርጥ አስታወቀ።

በደቡብ አፍሪካ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ኤችአይቪ በደማቸው ያለ ሲሆን፤ ቁጥሩ ከዓለም ከፍተኛው ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ድጋፍ ለማቋረጥ የተላለፈው ውሳኔ መነሻው ደቡብ አፍሪካ ነጭ ዜጎቿን "መጠበቅ አለመቻሏ" ነው።

ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን (አፍሪካነርስ) ከለላ አልተደረገላቸውም የሚለውን የአሜሪካ ክስ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚኒስቴር የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔውን እንዳላሳወቀው ጠቅሶ "ለረዥም ጊዜ ራሳችንን ለመቻል ዕቅድ ስናወጣ ነበር" ብሏል።

እስከ አውሮፓውያኑ 2025 ድረስ አሜሪካ ለደቡብ አፍሪካ የፀረ ኤችአይቪ ንቅናቄ በዓመት 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ትሰጥ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸው ሻክሯል።

ትራምፕ ሥልጣን እንደያዙ "በርካታ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች በቆዳ ቀለማቸው የተገለሉ የመሬት ባለቤቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን አባብሰዋል" ሲሉ ከስሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት 'ብላክ ኢኮኖሚክ ኢምፓወርመንት' የተባለው ፖሊሲው ከአፓርታይድ ዘመን አንስቶ የተንሰራፋውን የምጣኔ ሃብት አለመመጣጠንን ለማረም የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ ላይ ያስተላለፉት ውሳኔ ከነጭ ገበሬዎች ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም። ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ያቀረበችው ክስም አስቆጥቷቸዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከኢራን ጋር ትስስር አላት ብለውም ትራምፕ ይከስሳሉ።

ፕሬዝዳንቱ "ነጮች የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመባቸው ነው" ብለውም ሐሰተኛ መረጃ አሠራጭተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ለነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ስደተኞች በአፋጣኝ ጥገኛነት ለመስጠት መወሰኑን ደቡብ አፍሪካ መተቸቷ ይታወሳል።

የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ከደቡብ አፍሪካ የፀረ ኤችአይቪ መርሃ ግብር አንድ አምስተኛውን ይሸፍናል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ድጋፉን እንደሚያቋርጥ ይፋ አድርጓል።

"ደቡብ አፍሪካ [በአሜሪካ አስተዳደር] የተጠየቀችውን የፖሊሲ ማሻሻያ ስላላደረገች" ውሳኔው መተላለፉ ተገልጿል።

ደቡብ አፍሪካ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እንደመሆኗ በጤናው ዘርፍ "ራሷን እንድትችል" በሚል ከውሳኔ ላይ እንደተደረሰም አክሏል።

የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚኒስቴር እንዳለው፤ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ለፀረ ኤችአይቪ ንቅናቄው ሚና ቢኖረውም ነፍስ አድን የሆነው መድኃኒት ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ነው።

ከአንድ ዓመት በፊት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሲገናኙ ነጮች ላይ ደርሷል ስለተባለው መገለል በግልጽ መጠየቃቸውን ግንኙነታቸውን የበለጠ አጠልሽቶታል።

ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ኅዳር ባዘጋጀችው የቡድን 20 ጉባዔ ላይ አሜሪካ ሳትገኝ ቀርታለች።