ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጥበቃ በሚሰጠው ሕግ ዙሪያ ተከፋፍለዋል
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማክሰኞ ዕለት የማኅበራዊ ሚድያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊቀይር የሚችል ሂደትን ተመለከተ።
የ23 ዓመቷ ኖሄሚ ጎንዛሌዝ በፈረንጆቹ 2015 ፓሪስ ውስጥ በኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) መገደሏን ተከትሎ ቤተሰቡ ጉግልን በመክሰሱ ነው ጉዳዩ መታየት የጀመረው።
የጎንዛሌዝ ቤተሰብ የጉግል ንብረት የሆነው ዩቲዩብ የአሸባሪ ቡድኑ ቪዲዮዎችን ተጠቃሚዎች እንዲመለከቱ በመቀስቀስ ለጥፋቱ ተባባሪ ሆኗል ብለው ይከሳሉ።
ጉግል፤ አስርት ዓመታት ያስቆጠረ ሕግ በማጣቀስ ከደሙ ነፃ ነኝ ብሏል።
ኮሚዩኔኬሽንስ ዲሰንሲ አክት የተሰኘው ሕግ ቁጥር 230 የበይነ መረብ ኩባንያዎች ሌላ ሰው ለለጠፈው መልዕክት ተጠያቂ አይደሉም ይላል።
በፈረንጆቹ 1996 የወጣው ሕግ ኩባንያዎቹ ከአሠራራቸው የተፃረረ መልዕክት ካገኙ የማስወገድ መብት እንዳላቸውም ይጠቅሳል።
ማክሰኞ ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለሦስት ሰዓታት ገደማ የቆየ ችሎት አድምጧል።
የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናትን የሚወክሉ ጠበቆች፣ ጉግልና የጎንዛሌዝ ተወካዮች መከራከሪያቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ1996ቱን ሕግ ቁጥር 230 የተመለከተ ጉዳይ ሲመለከት ይህ የመጀሪያው ነው።
ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ እና ትዊተር ተጠቃሚዎቻቸው አንድን ምስል እንዲመለከቱ ሲያደርጉ ተጠያቂ ይሆናሉ ወይ የሚለውን አንገብጋቢ ጥያቄ ተነስቶበታል።
ችሎቱ የሁሉንም አካላት መከራከሪያ በሰማበት ወቅት የፍርድ ቤቱ ዳኞች፤ ሕጉ ከወጣ 27 ዓመታት አልፎታል ነገር ግን አሁን ያለው የበይነ መረብ ገጽታ ተለውጧል ሲሉ ተሰምተዋል።
ዳኞቹ፤ ፍርዱ ለጎንዛሌዝ ቤተሰብ የሚያደላ ከሆነ ደግሞ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩብንያዎች በክስ ይጨናነቃሉ የሚል ስጋት አላቸው።
ሊበራል ናቸው የሚባሉት ዳኛ ኤሌና ኬጋን “የክስ ዓለም እየፈጠራችሁ ነው” ብለዋል።
ወግ አጥባቂው ዳኛ ሳሙኤል አሊቶ እና ጥቁር አሜሪካዊቷ ኬታንጂ ብራውን ጃክሰን የጎንዛሌዝ ቤተሰብ ጠበቃዎች ባቀረቡት መከራከሪያ ግራ መጋባታቸውን ገልጠዋል።
ሌላኛው ወግ አጥባቂ ዳኛ ብሬት ካቫናህ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ያላቸው የሕግ ከለላ የሚያዳክም ውሳኔ “የዲጂታል ኢኮኖሚ ውድቀት ያመጣል” ብለዋል።
የጎንዛሌዝ ቤተሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉግልን የከሰሱት በፈረንጆቹ 2016 ነበር።
በወቅቱ ቤተሰቡ፤ ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የኢስላሚክ ስቴት ቪዲዮዎችን ለተመልካቾች እንዲደርስ በማድረግ የፌዴራል ፀረ-ሽብርተኝነት ሕግን ጥሷል ሲሉ ነበር የከሰሱት።
ነገር ግን ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በታች ያሉ ሁለት ፍርድ ቤቶች ጉግል በ1996 ሕግ ጥበቃ አለው ሲሉ ክሱን ውድቅ አድርገውታል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ውሳኔ ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ረቡዕ ዕለት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ትዊተር፤ ኢስላሚክ ስቴት የተሰኘው ቡድን አውታሩን እንዲጠቀም በመፍቀዱ ሽብርተኝነትን ደግፏል ወይ የሚል ጉዳይ ይመለከታሉ።