ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጊምቢውን ጥቃት የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች ሊመረምሩ መሆኑ ተነገረ
የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች በምዕራብ ኢትዮጵያ ጊምቢ ውስጥ በተፈጸመው ማንነትን የለየ ጅምላ ግድያ ዙሪያ ምርመራ ሊያደርጉ መሆናቸው ተነገረ።
ቅዳሜ፣ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በፈጸመው ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት አረጋግጧል።
ይህ በአገሪቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተፈጸሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶች መካከል የከፋው እንደሆነ በተነገረለት ጥቃት የተገደሉት ሰዎች አሃዝን የተለያዩ ወገኖች በተለያየ መጠን ሲገልጹት ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ሐሙስ ለጋዜጠኞች በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች 338 መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩባቸው የገጠር መንደሮች ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት መሆናቸው ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ከጥቃቱ የተረፉና ባለሥልጣናት ጭፍጨፋውን የፈጸሙት መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ።
ቡድኑ ግን ግድያውን አለመፈጸሙን በማስተባበል በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግበት ጠይቋል።
ጥቃቱን ተከትሎ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ተቋም ባሻገር፣ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ጭፍጨፋውን እንዲመረምሩ መሰየሙ ተገልጿል።
በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ የሚመረምረው ቡድን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ተፈጽመዋል የተባሉ ጥሰቶችንም ይመረምራል።
ኮሚሽኑ እንዳለው እየተከሰተ ያለው ጥቃት በአገሪቱ “ሊከሰቱ ለሚችሉ ተጨማሪ ጭፍጨፋዎች ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ” ነው ብሏል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ከተከሰተው በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል “በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ እንዲያቀርብ” ማዘዙ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንም በምዕራብ ወለጋው ጭፍጨፋ ወቅት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች በታጣቂዎቹ ታግተው መወሰዳቸውን አመልክቶ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በጥቃቱ ዙሪያ ፈጣን፣ገለልተኛና ዝርዝር ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቀው ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙት ጉቱ፣ ጨቆርሳ፣ ስልሳው፣ በገኔ፣ ጫካ ሰፈር እና ሀያው በተባሉ መንደሮች (ጎጦች) በታጣቂዎች በተፈጸመ ጭፍጨፋ አሶሽየትድ ፕሬስ በአሜሪካ የአማራ ማኅበርን ጠቅሶ እስካሁን 503 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።
ማኅበሩ እንደሚለው በጭፍጨፋው 503 ሰዎች መገደላቸውን ከምንጮቹ ማረጋገጡን አመልክቶ፣ ከእነዚህም መካከል የ399 ሰዎችን በስም እንደለየና የሞቱት ሰዎች ብዛት ግን ወደ 600 መቶ እንደሚጠጋ ለቢቢሲ ገልጿል።
በጥቃቱ ከተገደሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በርካታ ቤቶች ተቃጥለው የነዋሪዎች ንብረቶች ተዘርፈዋል።