ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋና ለሩሲያው ቫግነር የድጋፍ ሰልፍ አስተባብረዋል የተባሉ ክስ ተመሰረተባቸው
በጋና ለሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር የድጋፍ ሰልፍ አስተባብረዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።
ፖሊስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተዘጋጀውን የድጋፍ ሰልፍ የመሩ ናቸው ባላቸው አምስት ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን አረጋግጧል።
በጋና ደቡባ ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው ታኳሪዲ ግዛት ጥቂት ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ የተካሄደው የቫግነሩ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በአውሮፕላን መከስከስ ሕይወቱ ከማለፉ 10 ቀናት ቀደም ብሎ ነበር።
በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች የቫግነር ቅጥረኛ ቡደንን መለያ ከነቴራ አጥልቀው እና የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ እንደነበር የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቫግነር እንደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ፣ ሊቢያና ማሊ ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ ስምሪት አለው።
በጋና ሰለፉን እንዳዘጋጁ የተጠረጠሩ ሰዎች በሚቀጥለው ሳምንታት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን የቀረበባቸው ክስ ይዘት በተመለከተ ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ባለፈው ነሀሴ ወር የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ዋግነር) መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት የነበረው አውሮፕላን መከስከሱ ይታወሳል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ አጋር የነበረው ፕሪጎዢን የሚመራው ቅጥረኛ ወታደራዊ ኩባንያውም በዩክሬን ጦርነት ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ኢምብራየር ሌጋሲ የተሰኘው አውሮፕላን ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሲበር እንደነበር የሩሲያ አቪዬሽን ባለስልጣናት እታውቀው ነበር።
አውሮፕላኑም በሰሜናዊ ሞስኮ በሚገኘው ቴቨር ክልል የመከስከስ አደጋ እንዳጋጠመውም ባለስልጣናቱ አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ከቫግነር ጋር ግንኙነት ያለው ግሬይ ዞን የተሰኘው የቴሌግራም ገጽ ጄቱ በሩሲያ ጦር ተመትቶ መውደቁን ዘግቧል።
በጋና ይህ ከመሆኑ 10 ቀናት አስድሞ ነበር ጥቂት ሰልፈኞች ደጋፍ ለማድረግ አደባባይ የወጡት።