ትራምፕ በቤታቸው ደብቀውታል የተባለውን ምሥጢራዊ ዶሴ የሚመረምሩ ዳኛ ተሾሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ሲለቁ ወደ መኖርያ ቤታቸው አሸሽተውታል የተባለን ምሥጢራዊ ዶሴ እንዲመረምሩ ልዩ ዳኛ ተሾሙ።
ይህን ጉዳይ እንዲያዩ የተመረጡት ዳኛ ሬይመን ዲሪ የ78 ዓመት አዛውንት ናቸው።
ሬይመን ዲሪ ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እንዲመረምሩት የተመደቡት በዶናልድ ትራምፕ ጠበቆች የገለልተኝነት ጥያቄ በመነሳቱ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ የአገር ምሥጢር የታጨቀባቸውና ሥልጣን ሲለቁ ወደ ብሔራዊ የሰነዶች ግምጃ ቤት ማስረከብ የነበረባቸውን ሰነዶች ፍሎሪዳ፣ ማሮ-ላጎ መኖርያ ቤታቸው አሽሽተዋል በሚል ፖሊስ ብርበራ ማድረጉ ይታወሳል።
ፖሊስ ዶሴዎቹን ከማሮ-ላጎ ምድር ቤት ሰብስቦ ይዞ ከሄደ በኋላ የዶናልድ ትራምፕ ጠበቆች ሁለት ጥያቄ አንስተው ነበር።
ከነዚህ አንዱ የአሜሪካ ምርመራ ቢሮ ሰነዱን መመርመር እንዲያቆም የሚጠይቅ ነው።
ሁለተኛው ጥያቄ የነበረው ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ይታይልን የሚል ነበር።
በዶናልድ ትራምፕ ሰዎች ዘንድ ይህ የፍትሕ ሚኒስቴር አካሄድ የዲሞክራቶች ሴራ ነው ብለው ይጠረጥራሉ።
ትራምፕ በመጪው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይወዳደሩ ለማሰናከል ሆን ተብሎ የተሸረበ ነው በሚል ክስ አቅርበውም ነበር።
አሁን የተመረጡት ዳኛ ሬይመን ዴሪ ሰነዶቹን ከኤፍቢአይ ወስደው መርምረው ውሳኔ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ውሳኔው የአሜሪካ ምርመራ ቢሮ ሰነዶቹን መመርመሩን ይቀጥል ወይስ አይቀጥል የሚል ይሆናል።
እኚህ ዳኛ ጉዳዩን እንዲያዩ ሐሳብ ያቀረቡት የትራምፕ ጠበቆች ናቸው።
የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴርም በቀረበው ሐሳብ ተቃውሞ እንደሌለው ገልጧል።
ይሁንና የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ሰነዱ ከኤፍቢአይ እጅ እንዲወጣ የትራምፕ ሰዎች እየወተወቱ ያሉት ምርመራውን ለማደናቀፍ ነው በሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ባለሥልጣናቱ ትራምፕ ወደ ፍሎሪዳ ቤታቸው ይዘዋቸው የሄዱት ሰነዶች ብሔራዊ ቤተ መዛግብት መቀመጥ ነበረባቸው ብለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሥልጣን ሲለቁ እጃቸው የሚገኙ ከፍ ያሉ ብሔራዊ ምሥጢሮችን ወደ መዛግብት ቤት ማስረከብ ይኖርባቸዋል።
ትራምፕ እያሉ ያሉት ግን ወደ ማሮ-ላጎ መኖርያ ቤቴ ይዣቸው የሄድኳቸው ዶሴዎች በሙሉ የአገር ምሥጢራዊነታቸው ያበቃ ነው።
በዚህ ወር መጀመርያ አንድ የአሜሪካ ፌዴራል ዳኛ ትራምፕ ያቀረቡትን አቤቱታ በመስማት በኤፍቢአይ የተያዙ ሰነዶች ለጊዜው ምርመራቸው እንዲቆም አዘው ነበር።
ይህም የሆነው አንድ ጉዳዩን የሚያይ ገለልተኛ ዳኛ እስኪመደብ ነበር።
ትናንት ሐሙስ የፌዴራል ዳኛ የሆኑት ኤሊን ካነን ዳኛ ዴሪን በዚህ ጉዳይ ላይ ሾመዋቸዋል።
አክለውም የፍትሕ ሚኒስቴር ይህን ዶሴ በተመለከተ ምርመራውን እንዲያቆም አዘዋል።
ይህም ማለት የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ይህን ወንጀል ብሎ የጠረጠረውን ድርጊት ለጊዜው መመርመር እንዲያቆም ይገደዳል።
ምርመራውን የሚቀጥለው ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እንዲመረምሩት የተመደቡት ዳኛ ዶሴው እንዲመረመር ፍቃድ ሲሰጡ ብቻ ነው።
አሁን የተመደቡት ዳኛ ጉዳዩን በምን ያህል ጊዜ መርምረው ውሳኔ ይሰጣሉ የሚለው ይፋ አልተደረገም።
ፖሊስ ፍሎሪዳ የሚገኘውን የዶናልድ ትራምፕ መኖርያ ቤት በድንገት ደርሶ ብርበራ ያደረገው በፈረንጆቹ ኦገስት 8 ነበር።












