‘ለሰከንዶች ራሴን ስቼ ነበር’ ትራምፕ፣ ኤሎን መስክ በተገኘበት የፖለቲካ ቅስቀሳ አካሄዱ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ በፔንሴልቬኒያ ግዛት፣ በትለር ከተማ ድጋሚ የምረጡኝ ቅስቀሳ አደረጉ።

ይህ የሆነው በዚያች ከተማ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው ከሦስት ወር በኋላ ነው።

ትራምፕ ከሦስት ወራት በፊት በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ጥይት ጆሯቸውን ጨርፎት ነበር ያለፈው።

ከጀርባቸው ቆሞ የነበረ አንድ ግለሰብ በግድያ ሙከራው የተገደለ ሲሆን ሁለት ሌሎች ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ለሟቹ ግለሰብ የኅሊና ጸሎት ያደረጉ ሲሆን ድጋሚ የመጣሁት ለናንተ ለአሜሪካዊያን ዋጋ ለመክፈል ምን ያህል ርቀት እንደምሄድ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።

በዚህ ወሳኝ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዶናልድ ትራምፕ በምክትላቸው ጄዲ ቫንስ እና በቢሊየነሩ ኤለን መስክ ታጅበው ነበር።

በዚህ በበትለር-ፔንሴልቬኒያ በተካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ የሲክሬት ሰርቪስ ጥበቃ ከፍተኛ የተባለ ደኅንነት ያሰማራ ሲሆን አካባቢው በድሮንና በስናይፐር ተኳሾች ተሞልቶ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ትራምፕ ንግግር የሚያደርጉበት አትሮንስ ፊትለፊት ጥይት የማይበሳው መስታወት እንዲጋረድ ሆኖ ነበር።

ትራምፕ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ያኔ ጥይት የሳታቸው ቅጽበት አስታውሰው፤ ’ለ15 ሰከንዶች ጊዜ ቆሞ ነበር’ ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፔንሴልቬኒያ የመጡት ይህን ግዛት ማሸነፍ በፕሬዝዳንትነት ለመመረጥ እጅግ ወሳኝ ስለሆነ ነው።

በአሜሪካ ምርጫ መጪውን ፕሬዝዳንት ለመወሰን ሰባት ግዛቶች ከተቀሩት 47 ግዛቶች የበለጠ ወሳኝ ሚና አላቸው።

ለዚህም ነው በተለምዶ 'ወላዋይ ግዛቶች' (Swing states) በመባል የሚጠሩት ሰባቱ ግዛቶች ላይ ሁለቱም እጩዎች ማለትም ካማላ ሐሪስና ዶናልድ ትራምፕ በየፊናቸው ከፍተኛና የማያቋርጥ የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ የሚገኙት።

ምንም እንኳ በዚህ ምርጫ 270 ሚሊዮን አሜሪካዊያን ቀጣይ ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ ለመስጠት ብቁ ቢሆኑም ፕሬዝዳንቱን የሚወስኑት መራጮች የሚገኙት ግን በነዚህ ’ወላዋይ ግዛቶች’ ውስጥ ነው።

ጆርጂያ፣ ሚሺጋን፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ አሪዞና፣ ዊስኮንሰን፣ ኔቫዳና ትናንት ትራምፕ ቅስቀሳ ያደረጉባት ፔንሲልቬኒያ ለመጪው ምርጫ ማሸነፍ ቁልፍ ግዛቶች ናቸው።

በሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች መሠረት በነዚህ ሰባት ግዛቶች ካመላ ሐሪስና ዶናልድ ትራምፕ ብዙም የማይራራቅ ድምጽ ነው ያላቸው።

ለዚህም ይመስላል ይህ የአሜሪካ ምርጫ በታሪክ ከፍተኛ ፉክክርና ትንቅንቅ የሚታይበት ነው ተብሎ የሚጠበቀው።

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ

ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በነበራቸው ቅስቀሳ ስለ ግድያ ሙከራ አድራጊው ንግግር አድርገዋል። “ይህ መሰሪ ሰይጣን ሊገድለኝ ቢሞክርም አልሠመረለትም፤ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን" ብለዋል።

ትራምፕ ከዚህ የግድያ ሙከራ በኋላ ባለፈው ወር በፍሎሪዳ ግዛት፣ ፓልም ቢች ጎልፍ ክለብ አንድ ግለሰብ አድብቶ ሊገድላቸው ሲሰናዳ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወሳል።

በትናንቱ የበትለር ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ልጃቸው ኤሪክ ትራምፕ እና ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ተገኝተው ነበር።

ትራምፕ በአወዛጋቢ አስተያየቱ የሚታወቀውን ቢሊየነሩን ኤለን መስክን ለማመስገን ወደ መድረክ የጋበዙት ሲሆን እሱም አጭር ንግግር አድርጓል።

“በእኔ እምነት ይህ ምርጫ በታሪክ እጅግ ወሳኙ ነው። ድምጻችሁን ለትራምፕ ስጡ” ሲል ተናግሯል።

በዚህ የበትለሩ የምርጫ ቅስቀሳ ትራምፕን በድጋሚ የሚሉትን ለመስማት ከ25ሺህ ሰው ያላነሰ ተገኝቷል።

ትራምፕ እንደተመለደው ጆ ባይደንና ካመላ ሐሪስን የወረፉ ሲሆን “አገራችንን በዱሪዬ መጤዎች” አስወርረዋል በሚል ከሰዋቸዋል።

በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ያለው ስደተኛ ወደ አሜሪካ በገፍ መግባቱን ያወሱት ትራምፕ ለዚህም ዲሞክራቶችን ወቅሰዋል።

“ወንጀል በርክቷል፣ የአሜሪካ ክብር ወድቋል፣ በወንበዴ ስደተኞች ተወረናል፣ ክብራቸሁን የማስመልሰው ብቸኛው ሰው እኔ ብቻ ነኝ" ብለዋል፤ ትራምፕ በትናንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት።

ለአሜሪካ ምርጫ ቀን አንድ ወር ብቻ ነው የቀረው።