“ሩሲያ በዩክሬን መሸነፍ ቢኖርባትም መጨፍለቅ የለባትም" ፕሬዚዳንት ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሩሲያ በዩክሬን መሸነፍ እንዳለባት ቢያምኑም መጨፍለቋን ግን እንደማይፈልጉ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንት ማክሮን ምዕራባውያን ሃገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲጨምሩ አሳስበው ሃገራቸው ለተራዘመ ጦርነት መዘጋጀቷንም ለፈረንሳዩ ሚዲያ ገልጸዋል።
"ሩሲያ በዩክሬን እንድትሸነፍ እንዲሁም ዩክሬን ራሷን እንድትከላከል እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ነገር ግን ጦርነቱ ወደ ሩሲያ ተዛምቶ ሃገሪቱን መጨፍፈለቅ እና መደምሰስ ይገባል የሚሉ እሳቤዎችን ተቃውመዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮንን ጨምሮ በርካታ መሪዎች በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ወደ ዩክሬን የሚደረገውን የጦር መሳሪያ አቅርቦትን ማፋጠን እንዲሁም በሞስኮ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብም ለመጣል ቃል ገብተዋል።
“አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሩሲያን በገዛ መሬቷ ላይ ላይ በማጥቃት ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ወይም መጨፍለቅ አለብን የሚሉትን አላምንበትም” ሲሉ ማክሮን ለ ጆርናል ዱ ዲማንቼ ለተሰኘው የፈረንሳዩ ጋዜጣ ተናግረዋል።
“እነዚህ ታዛቡዎች ከሁሉም በላይ ሩሲያን የመጨፍለቅ ፍላጎት አላቸው። ይህ መቼም የፈረንሳይ አቋም ሆኖ አያውቅም፤ ለወደፊቱም ፍጹም አይሆንም” ማለታቸውም ሰፍሯል።
አርብ ዕለት በሙኒክ በነበረው ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ማክሮን ከሞስኮ ጋር ለመወያየት ጊዜው አሁን አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።
ሆኖም የሰላም ውይይትና፣ ድርድሮች የመጨረሻው ግብ መሆናቸውንም ከመጥቀስ ወደ ኋላ አላሉም።
ፕሬዚዳንቱ በምዕራባውያን አጋሮች የሚደገፉት የዩክሬን ወታደራዊ ጥረቶች “ሩሲያን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ እና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት” ብቸኛው መንገድ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
በሩሲያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ማድረግ የሚለውን እሳቤ ያጣጣሉት ፕሬዚዳንት ማክሮን በዓለም ዙሪያ ተመሳሳይ ጥረቶች እንዳልተሳኩ አስታውሰዋል።
ምንም እንኳን ፕሬዚዳንት ማክሮን በውይይት ላይ በጎ አስተያየታቸውን ቢሰጡም ድርድር ለዩክሬን መሪዎች ሩቅ መሆኑ ተነግሯል።
አርብ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ሩሲያን ወደ ሙኒክ ላለመጋበዝ የተላለፈውን ውሳኔ በበጎ ተቀብለውታል።
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከሩስያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሊወያዩ እንደማይችሉ ገልጸው “በሃገራቱ መካከል መተማመን የለም” ሲሉ አስረግጠዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ የዩክሬንን ግዛት አሳልፎ መስጠት የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮን ከዚህ ቀደም በዩክሬን ላይ በሰጡት የተለያዩ አስተያየቶች ከአንዳንድ የኔቶ አጋሮች ትችቶችን እንዲያስተናግዱ ምክንያት ሆኗል።
ባለፈው ዓመት ሩሲያ “በዩክሬን በፈጸመችው ወረራ መዋረድ (መሸማቀቅ) ሊሰማት አይገባም” ብለው ነበር።












