‘ሩሲያ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎችን ፈጽማለች’ አሜሪካ

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ወረራ ምክንያት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መፈጸሟን አሜሪካ አስታወቀች።

አሜሪካ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መሆናቸውን በይፋ ማወጇንም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ተናግረዋል።

ሩሲያ በዩክሬን “ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፣ ስቅይት፣ መድፈር እና የማፈናቀል ድርጊቶች ፈፅማለች” ሲሉም ምክትል ፕሬዝዳንቷ በሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።

በጉባዔው ላይ የተገኙት የዓለም መሪዎች ለዩክሬን ዘላቂ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ለዩክሬን የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍን “በከፍተኛ ሁኔታ” የምንጨምርበት ወቅት ነው ብለዋል።

ምዕራባውያን አጋሮች ለዩክሬንን የወደፊት የደኅንነት ሁኔታንም ለማስጠበቅ ማቀድ መጀመር እንዳለባቸው እና አገሪቱ ራሷን እንድትከላከል አስፈላጊው የጦር መሳሪያ ሊቀርብላት ይገባል ብለዋል።

በጀርመን የተካሄደው ጉባኤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀረው ጊዜ ነው።

ዩክሬን ውስጥ መጠነ ሰፊ ጥሰት የፈጸሙት የሩሲያ ወንጀለኞችም ተጠያቂነታቸው ሊረጋገጥ ይገባል ሲሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ በጉባዔው ላይ አፅንኦት ሰጥተዋል።

“ድርጊቱ በጋራ እሴቶቻችን እና በሰብዓዊነታችን ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሲቪል ሕዝብ ላይ “መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ወይም መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የሚፈጸም ጥቃት” ሲል ይፈርጀዋል።

ሩሲያ በበኩሏ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ አላደረግኩም ስትል በተደጋጋሚ ማስተባበሏ ይታወሳል።

“በዩክሬን ውስጥ የሩሲያ ድርጊትን በተመለከተ ያሉትን ማስረጃዎችን መርምረናል። ወንጀሎቹን በተመለከተ ሕጉ የሚለውን እናውቃለን። እናም ምንም ጥርጥር የለውም እነዚህ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው” ሲሉ የቀድሞ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ ሃሪስ ለጉባኤው ተናግረዋል።

ካማላ በዩክሬን ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ “አረመኔያዊ እና ኢሰብዓዊ” ድርጊቶችንም ጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል በቡቻ የተገኙ የጅምላ መቃብሮችን እንዲሁም በማሪዩፖል በሚገኝ ቲያትር ቤት የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃትን አንስተዋል።

በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚዳኙት በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ነው።

ነገር ግን አይሲሲ ተጠርጣሪዎችን የማሰር ሥልጣን የለውም። ሥልጣኑም ፍርድ ቤቱን ባቋቋሙና ስምምነቱን በፈረሙ አገራት ውስጥ ብቻ የተወሰነ ነው።

ነገር ግን ሩሲያ የዚህ ስምምነት ፈራሚ አይደለችም፤ ስለዚህ ማንኛውም ተጠርጣሪዎች ተላልፈው የመሰጠት ዕድላቸው የመነመነ ነው።