ሰሜን ኮሪያ አሜሪካንን እና ደቡብ ኮሪያን ለማስጠንቀቅ የሚሳኤል ሙከራ አደረገች

ሰሜን ኮሪያ በወታደራዊ ትርኢት ወቅት ለዕይታ የቀረበቻቸው የሚሳኤል ማስወንጨፊያዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ በወታደራዊ ትርኢት ወቅት ለዕይታ የቀረበቻቸው የሚሳኤል ማስወንጨፊያዎች
ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ ባላንጣዎቿን ለማስጠንቀቅ ያሏትን አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች አስተማማኝነት ለመፈተሽ በሚል ድንገተኛ ሙከራ ቅዳሜ ዕለት ማድረጓን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

የተተኮሰው ሚሳኤል ለ67 ደቂቃዎች እና ከ900 ኪሎ ሜትሮች በላይ ከተጓዘ በኋላ ከጃፓን ባሕር ላይ ወድቋል።

ሙከራው ሰሜን ኮሪያ አሜሪካንን እና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ ጠላት ኃይሎችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ሚሳኤሉ እንዳለው ያሳየ መሆኑን አገሪቱ ገልጻለች።

ይህ የሚሳኤል ሙከራ የተካሄደው ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ፣ ከሰሜን ኮሪያ በኩል እየጨመረ የመጣውን የኑክሌር ስጋት ለመቋቋም በሚል በሚቀጥለው ወር ለማካሄድ ካቀዱት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ቀደም ብሎ ነው።

የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት እንዲህ ያለው ወታደራዊ ልምምድ ወረራ ለመፈጸም የሚደረግ ዝግጅት ነው ብለው እንደሚያስቡ እና ለዚህ የጦር እንቅስቃሴ ደግሞ “ታይቶ የማይታወቅ ጠንካራ” አጸፋን አገራቸው ትሰጣለች ብለዋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ኦ-ጆንግም ይህንን የአገራቸውን አቋም በማጠናከር፣ ማንኛውም በሰሜን ኮሪያ ላይ የሚፈጸም ጠብ ጫሪ ተግባር “ጠንካራና ግዙፍ” ምላሽ ይጠብቀዋል በማለት ቅዳሜ ጠዋት ተናግረው፣ አሜሪካ በአገራቸው ላይ የደቀነችውን “ስጋት” እንድታስወግድ አሳስበዋል።

ጨምረው ግን የደቡብ ኮሪያዋ ዋና ከተማ ሴዑል የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎች ኢላማ እንደማትሆን ገልጸዋል።

ባለፈው አርብ ሰሜን ኮሪያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች የተካተቱበት ወታደራዊ ኃይሏን የሚያሳይ ግዙፍ ትርኢት አቅርባ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቅዳሜ ዕለቱ የሚሳኤል ሙከራ ጃፓን የምጣኔ ሃብት ልዩ ቀጠና ብላ በምትጠራው አካባቢ መውደቁን የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ አረጋግጠዋል።

እነዚህ የሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች በሰሜን ኮሪያ ዙሪያ ካሉ አገራት ባሻገር ረጅም ርቀት በመጓዝ የአሜሪካ ግዛቶችን ጭምር የመምታት አቅም ስላላቸው አሳሳቢ ሆነዋል።

የጃፓን የመከላከያ ሚኒስትር ሃማዳ ያሱካዙ ቅዳሜ ዕለት እንደተናገሩት ሚሳኤሉ 14,000 ኪሎ ሜትሮች መጓዝ ስለሚችል በርቀት ላይ ያሉ አካባቢዎችን ሊመታ ይችላል።

“ሰሜን ኮሪያ በተከታታይ እየፈጸመቻቸው ያሉ ተግባራት የጃፓንን እንዲሁም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሰላም እና መረጋጋት ስጋት ላይ የጣለ በመሆኑ ፈጽሞ ይቅር የሚባል አይደለም” ብለዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ።

ይህንን የሰሜን ኮሪያን ድርጊት “ግድየለሽ ባህሪይ” በማለት ያወገዙት ደግሞ ጀርመን ውስጥ ስብሰባ ላይ የሚገኙት የቡድን ሰባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ናቸው።

ባወጡት መግለጫ ላይም የሚሳኤል ሙከራው “አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰላም እና ደኅንነትን” አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገዋል ብለዋል።

የደቡብ ኮሪያ ጦር እንዳመለከተው ሚሳኤሉ የተወነጨፈው ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በስተ ሰሜን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከሚገኝበት ሱናን ከተባለ ስፍራ ነው። በተጨማሪም ይህ ቦታ በቅርቡ የተደረጉ አህጉር አቋራጭ የሚሳኤል ሙከራዎች የተተካሄዱበት መሆኑ ተገልጿል።

የሰሜን ኮሪያ የተወንጫፊ እና የኑክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራሞች በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ዕገዳ የተጣለባቸው ቢሆንም፣ ይህ ግን ፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያ ግንባታዋን ከመቀጠል እና ያላትን ወታደራዊ አቅም ለማሳየት ትርኢቶችን ከማካሄድ አላገዳትም።

ከሁለት ሳምንት በፊት የአገሪቱ መሪ ኪም ጆን-ኡን በታደሙበት ባልተለመደ ሁኔታ እኩለ ሌሊት ላይ በተካሄደ ወታደራዊ ትርኢት፣ ሰሜን ኮሪያ አስካሁን ከታዩት በበለጠ ያሏትን አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን አሳይታለች።