ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የልቅ ወሲብ ተዋናይትን ዝም ለማሰኘት ፈጽመውታል በተባለው ክፍያ ሊከሰሱ ነው
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የልቅ የወሲብ ፊልም ተዋናይትን ዝም ለማሰኘት በከፈሉት ገንዘብ የወንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው ነው።
የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ የቀረበባቸው የክስ ዝርዝር እስካሁን ይፋ ባይደረግም፤ ትራምፕ ስቶርሚ ዳንኤልስ ለተባለችው ሴት 130ሺህ የአሜሪካ ዶላር መክፈላቸው ተገልጿል።
የ76 ዓመቱ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት እአአ 2016 ላይ ፈጽመውታል የተባለውን ክፍያ አምነው አልተቀበሉም።
በአሜሪካ ታሪክ በሥልጣን ላይ ያለም ይሁን በቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ የወንጀል ክስ ተመስርቶ አያውቅም።
የትራምፕን ጉዳይ ሲመረምሩ የቆዩት ዳኞች ስቶርሚ ዳንኤልስ ከቀድሞ ፕሬዝዳንት ጋር ስላላት ግንኙነት ዝምታን እንድትመርጥ ትራምፕ ክፍያ ፈጽመዋል መባሉን ከመረመሩ በኋላ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ ክስ እንዲመሰረትባቸው ወስነዋል።
በትራምፕ ላይ የተቀረበውን ክስ ሲመሩ የቆዩት የማንሃተን ዐቃቤ ሕግ አልቪን ብራግ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በቁጥጥር ስለሚውሉበት ሁኔታ ከትራምፕ ጠበቆች ጋር ንግግር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ሲቢኤ ኒውስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው ነዋሪነታቸውን ፍሎሪዳ ያደረጉት ትራምፕ ዛሬ ሰኞ ወደ ኒው ዮርክ ከበረሩ በኋላ ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው የቀረበባቸው ክስ ይነበብላቸዋል።
ትራምፕ በፖሊስ ተይዘው የጣት አሻራቸውን ይሰጣሉ እንዲሁም እንደሌሎች በወንጀል ተከሳሾች ሁሉ ፎቶግራፋቸው በፖሊስ ይነሳል።
ትራምፕ የቀረበባቸውን ክስ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለው ነው ከማለት አልፈው እርሳቸው ላይ የቀረበባቸውን ክስ እየመሩ ያሉትን የኒው ዮርክ ዐቃቤ ሕግ የጆ ባይደንን "ቆሻሻ ሥራ እየሰራ ያለ ሰው ነው" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
የጆ ባይደን አስተዳደር የቀጣዩን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማስቀየር ይህን ክስ እንዳቀረቡባቸው ትራምፕ በጽሑፍ መግለጫቸው ገልጸዋል።
ትራምፕ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የትራምፕ ጠበቃ ሱሳን ኔችልስ ደንበኛቸው ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸሙም ያሉ ሲሆን “በፍርድ ቤት ይህን ፖለቲካዊ ክስ አጥብቀን እንታገላለን” ብለዋል ጠበቃዋ።
ትራምፕ ጉዳያቸው እየታየ ያለው ከእአአ 2016 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊደረግ ሁለት ሳምንታት ሲቀሩት ከቀድሞ የልቅ ወሲብ ፊልም ተዋናይት ስቶርሚ ዳንኤልስ ጋር አላቸው ስለተባለው ግንኙነት ምንም እንዳትናገር በቀድሞ ጠበቃቸው ማይክል ኮሀን አማካይነት ክፍያ ፈጽመዋል ከተባለ በኋላ ነው።
ስቶርሚ ዳንኤልስ በበኩሏ ትራምፕ ከአሁኗን ባለቤታቸው ሜላኒያ ጋር ትዳር ከመሰረቱ ከአንድ ዓመት በኋላ እአአ 2006 ላይ ግንኙነት ፈጽመናል ብላለች።
የቀድሞ የትራምፕ ጠበቃም በትራምፕ ትዕዛዝ 130ሺህ ዶላሩን ፈጽሚያለሁ ሲል ፍርድ ቤት ተናግሯል። የትራምፕ የቀድሞ ጠበቃ ማይከል ኮሀን በትራምፕ አስተዳደር ወቅት የተለያዩ የወንጀል ክሶች ቀርበውበት ከ2018 እስከ 2020 ድረስ በእስር ቆይቶ ነበር።
ይህን ትረምፕ ላይ የቀረበው ክስ የ2024 የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድድር ላይ ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል። ትራምፕ ሪፓብሊካን ፓርቲ ወክለው ወደ ዋይት ሃውስ ለመመለስ አንዱ ተፎካካሪ ናቸው።
ይሁን እንጂ በአሜሪካ ሕግ በወንጀል ክስ ጥፋተኛ የተባለም ይሁን እስር ተፈርዶበት እስር ቤት ያለ ፖለቲከኛ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እና ፕሬዝዳንት ሆኖ ማገልገልን የሚከለክል አንቀጽ የለም።